ሩሲያ ዶንባስክ በተሰኘው የዩክሬን ግዛት ሙሉ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯን አስታውቃለች
ሩሲያ ዶንባስክ በተሰኘው የዩክሬን ግዛት ሙሉ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯንና ዩክሬንም ለአንድ ወር የሚዘልቅ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጀመሯን ተከትሎ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተለያዩ አስተያየቶችን እየሠጠ እና አቋሙን እየገለጸ ይገኛል፡፡
አል ዐይን አማርኛም ዋና ዋናዎቹን ማለትም በዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ተቋማት እንዲሁም በሃገራት መሪዎች የተሰጡ አስተያየቶችን በተከታዩ መንገድ በአጭሩ አጠናቅሯቸዋል፡፡
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ፣ የተመድ ዋና ጸሃፊ
“እባካችሁ በሰብዓዊነት ስም እማጸናችኋለሁ፤ ከባለፉት 100 ዓመታት ወዲህ በአውሮፓ እጅግ አስከፊ የሆነው ጦርነት እንዲጀመር አትፍቀዱ”
“መቆም አለበት በስልጣን ዘመኔ እጅግ አስከፊው ቀን ነው”
ኡርሱላ ቮንደ ለየን ፣ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት
“ድርጊቱን እናወግዛለን፤ ፑቲን ነው አውሮፓን ድጋሚ ወደ ጦርነት የከተተው፡፡ ከዩክሬናውያን ጎን ነን፡፡ ሩሲያ በህብረቱ ሃገራት በምታንቀሳቅሰው ሃብት ላይ ከባድ ማዕቀብ እንጥላለን፡፡”
ጆሴፍ ቦሬል፣ የአውሮፓ ህብረት ምክትል ፕሬዝዳንት፣ የውጭ ጉዳይ እና ደህንነት ጉዳዮች ኃላፊ
“ይህ የአውሮፓ ወይ የዲፕሎማሲ ጉዳይ አይደለም፤ ይልቁንም የህልውና፤ የመላው ዓለም ጉዳይ ነው፡፡ ሩሲያ የማትጠብቀው መገለል ይጠብቃታል፤ ከባድ ማዕቀብም እንጥላለን”
ጆ ባይደን ፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት
“ሩሲያ በዩክሬናውያን ላይ በጀመረችው ጦርነት ለሚደርሰው ጉዳት ኃላፊነቱን ትወስዳለች፤ ዓለምም ተጠያቂ ያደርጋታል”
ቦሪስ ጆንሰን ፣ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር
“ፑቲን ደም መፋሰስንና ውድመትን መርጧል፤ ጠንካራ አጸፋዊ ምላሽ እንሰጣለን”
ኢማኑዔል ማክሮን፣ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት
“ሩሲያ የጀመረችውን ወታደራዊ ዘመቻው ልታቆም ይገባል፤ ከዩክሬናውያን ጎን ነን፤ ዘመቻው እንዲያበቃ ከአጋሮቻችንም ጋር እንሰራለን”
ጀስቲን ትሩዶ፣ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር
“ይህ በግልጽ የዩክሬንን ሉዓላዊነትና ግዛታዊ አንድነት እንዲሁም ሩሲያ የገባቻቸውን ዓለም አቀፍ ህግጋት መጣስ ነው”
ፉሚዎ ኪሺዳ ፣ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር
“ የሩሲያ ወረራ የዓለም ስርዓትን ከመሰረቱ የሚያናጋ ነው፤ የተናጠል እርምጃም ሁኔታውን አይቀይረውም”
ኋ ቹንዪንግ ፣ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ
“ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ከመውጣቱ በፊት ጥንቃቄ እንዲደረግ እናሳስባለን”
የሚሉ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡ አስተያየቶቹ ከተለያዩ አካላት የሚመጡ ናቸው፡፡ በስም ያልተጠቀሱ ሌሎችም የየራሳቸውን ሃሳብ በመሰንዘር ላይ ይገኛሉ፡፡ አል ዐይን አማርኛ ጦርነቱን የተመለከቱ ጉዳዮችን እየተከታተለ ያቀርባል፡፡