የሩሲያው ካፌ ባሰራጨው ማስታወቂያ ምክንያት ተጨናንቋል
በፕርም ከተማ የሚገኘው “ኮፊ ስማይል” ካፍቴሪያ “ከሰው ልጅ በሚገኝ ወተት ማኪያቶ እሰራለሁ” የሚል አነጋጋሪ ማስታወቂያ አስነግሯል
የማስታወቂያው ሃሳብ አፍላቂም ልጇን የምታጠባ የካፌው ደንበኛ ናት ተብሏል
በሩሲያዋ ፐርም ከተማ የሚገኝ ካፍቴሪያ ከሰሞኑ የማህበራዊ ሚዲያዎችን ትኩረት ስቧል።
“ኮፊ ስማይል” የሚል ስያሜ ያለውና በተለያዩ ከተሞች ቅርንጫፎችን የከፈተው ድርጅት በግዙፍ ሰሌዳዎች ላይ የለጠፈው ማስታወቂያ ነው መነጋገሪያ ርዕስ ያደረገው።
ካፌው “ከሰው ልጅ ጡት የሚገኝ ወተትን ተጠቅመን የምናዘጋጀውን ማኪያቶ ይሞክሩት” የሚል ማስታወቂያውን ሩሲያውያን በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲቀባበሉት ቆይተዋል።
የኮፊ ስማይል ባለቤት ማክሲም ኮቤልም “በልዩና በፋርማሲ ከረጢቶች የተጠራቀመ የጡት ወተትን ተጠቅመን ማኪያቶ እንሰራላችኋለን” የሚል የቪዲዮ ማስታወቂያ መልቀቁም ሩሲያውያንን በሁለት ከፍሏ።
አብዛኞቹ “ግነትና ውሸት የበዛበት ተራ ማስታወቂያ ነው” ሲሉ ሌሎች ደግሞ “እስኪ ሄደን እናረጋግጥ” በማለት ከድምዳሜ ይታቀባሉ።
የፐርም ከተማ አስተዳደርም ከአስገራሚው ማስታወቂያ በኋላ የህዝብ አስተያየትን ስብስቧል፤ 46 ከመቶ ምላሽ ሰጪዎች የጡት ወተት ማኪያቶውን በፍጹም አንቀምሰውም ያሉ ሲሆን፥ 23 በመቶው ግን ለመሞከር ችግር የለብንም ማለታቸውን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።
የሩሲያ የምግብ ደህንነት ባለስልጣን ጉዳዩን ይመረምር ዘንድም ጫናው በዝቶበታል።
ካፌው ይህን ማስታወቂያ እንዳስነገረ ባልጠበቀው መልኩ የደንበኞቹ ቁጥር መጨመራቸውን ባለቤቱ ማክሲም ኮቤል ይናገራል።
8 ዶላር ዋጋ የወጣለትን ማኪያቶ ለመጠጣት ከተለያዩ የሩሲያ ክፍሎች ወደ ኮፊ ስማይል መጉረፋቸውን በመጥቀስም “ማስታወቂያው ይህን ያህል ተጽዕኖ ይኖረዋል ብዬ አላመንኩም” ይላል።
በርካቶች በማስታወቂያ የተመለከቱትን ለመሞከር ካፌውን ቢጎበኙም እንደተጠረጠረው ለየት ያለው ማኪያቶ ግን ሊቀርብ አልቻለም።
የካፌው ባለቤት ኮቤል በሰጠው መግለጫ ፥ “በርግጥ ከመጀመሪያውኑ ከሴቶች ጡት ከሚገኝ ወተት ማኪያቶ ሰርተን ለማቅረብ አላሰብንም ፤ ህገወጥ ተግባር መሆኑን እናምናለን” ብሏል።
ካፌውን በቀላልና በርካሽ ዋጋ እንዴት ላስተዋውቀው ብሎ ሲያስብ ልጇን ከምታጠባ እናት ጋር የተገናኘው ኮቤል፥ አወዛጋቢውና በርካቶችን ያነጋገረው የማስታወቂያ ሃሳብ ከምታጠባው ሴት የተወሰደ መሆኑን ገልጿል።