የሞስኮን ወታደራዊ ሚስጢሮች አሳልፎ የሰጠው የሩሲያ ኮማንደር
ወታደራዊ አዛዡ በስልኩ ላይ የቀረጸው ተንቀሳቃሽ ምስል በማፈትለኩ ለከባድ ቅጣት ተዳርጓል
አዛዡ ስልኩ ሳይጠለፍ እንዳልቀረ አልያም የቅርብ ሰው አሳልፎ ሰጥቶታል ተብሏል
ዴኒስ ቫሌሪቪች የተባለ የሩሲያ አንድ ኮማንደር ሀገሪቱ ውስጥ ካሏት ወታደራዊ አመራሮች መካከል አንዱ ናቸው።
እኝህ ግለሰብ ከሰሞኑ ካረፉበት ሆቴል ሆነው በስልካቸው ተንቀሳቃሽ ምስል ቀርጸው የቅርብ አለቃቸው ፈቃድ እንዲሰጧቸው መልዕክት ይልካሉ።
ይሁንና ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል ለአለቃቸው ቢደርስም ሾልኮ ወጥቶ በማህበራዊ ሚዲያዎች መንሸራሸሩን ተከትሎ ጉዳዩ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
ኮማንደሩ የአለቃቸውን ስም እየጠሩ “ፈቃድ እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ፣ እባክህ ትንሽ ልተኛ፣ የነገው ስራችን ጥሩ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ፣ እስከ ከሰዓት ከተኛሁ ይበቃኛል” ሲሉ በመልዕክቱ ላይ ተሰምተዋል።
ኮማንደር ዴኒስ ለአለቃቸው ፈቃድ በጠየቁበት ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ከጀርባ ሁለት ወጣት እንስቶች ራቁታቸውን አልጋ ላይ መታየታቸው ነበር ብዙ ሩሲያዊያንን ያስቆጣው።
ምስሉ ለብዙዎች መድረሱን ተከትሎ በርካቶች በሩሲያ ጦር ላይ ትችቶችን የሰነዘሩ ሲሆን ዩክሬናዊያን ደግሞ የበለጠ በሞስኮ ላይ ተሳልቀዋል ሲል ሜይል ኦን ላየን ዘግቧል።
ይህን ተከትሎም ኮማንደር ዴኒስ ከሀላፊነት የተነሱ ሲሆን ተጨማሪ ከባድ ቅጣት እንደተጣለባቸው በዘገባው ላይ ተገልጿል።
ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ በዩክሬን ውጊያ ግንባር ላይ ያሉ የሩሲያ ወታደሮች የገና በዓልን ተሰባስበው በማክበር ላይ እያሉ አንድ ወታደር ተንቀሳቃሽ ስልክ ማብራቱን ተከትሎ በዩክሬን ሚሳኤል እይታ ውስጥ ገብተው በተሰነዘረ ጥቃት ከ500 በላይ ወታደሮች መገደላቸው ይታወሳል።
አሁን በተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል ምክንያት ከዩክሬን የተፈጸመ ጥቃት መኖሩ አለመኖሩ እስካሁን አልተገለጸም።
በኮማንደር ዴኒስ ስልክ የተቀረጸው ይፍ ተንቀሳቃሽ ምስል አፈትልኮ እንዴት ወደ ማህበራዊ ትስስር ገጾች እንደደረሰ እስካሁን በይፋ ያልተገለጸ ሲሆን ስልኩ ሳይጠለፍ አልቀረም ተብሏል።