ቻይና እና ሩሲያ ከአራት ሚሊዮን በላይ ወታደሮች አሏቸው
ሩሲያ እና ቻይና አዲስ ወታደራዊ ጥምረት መመስረታቸውን አስታወቁ።
በአሜሪካ የሚመራውን የዓለም ስርዓት ለመቀየር ህብረት መፍጠራቸውን የተናገሩት ሩሲያ እና ቻይና በወታደራዊ መስክም ትብብር መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
ሁለቱ ሀገራት አዲስ ወታደራዊ ትብብር መፍጠራቸውን እና በጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ ፣ የጋራ ወታደራዊ ትብብር በማድረግ እና ሌሎች ስራዎችን እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል ።
የቻይና መከላከያ ሚንስቴር የዓለም ሁለተኛው ግዙፍ ወታደራዊ አቅም ካላት ሩሲያ ጋር አዲስ ትብብር ፈጥረናል ብሏል።
ሁለቱ ሀገራት የጋራ ቅንጅት ከፈጠሩ ሊቋቋማቸው የሚችል ሀገር እና ተቋም እንደማይኖርም ነው ሚንስቴሩ ያስታወቀው።
ሁለቱ ሀገራት በወታደራዊ መረጃዎች ልውውጥ፣ ቴክኖሎጂ እና ሌሎችም ስትራቴጂካዊ ስምምነቶች ላይ ደርሰዋልም ተብሏል።
ሩሲያ እና ቻይና በጋራ ከአራት ሚሊዮን በላይ ወታደሮችን በመያዝ ከዓለም ቀዳሚዎች መሆናቸው ተገልጿል።
ሩሲያ በተናጥል 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ወታደሮች ሲኖራት ቻይና ደግሞ 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ወታደሮች አሏት ነው የተባለው።
የሁለቱ ሀገራት ዓመታዊ የመከላከያ በጀት ከ340 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሲሆን ይህም በዓለም ላይ ከፍተኛው ወታደራዊ በጀት ነው።
ከዩክሬን ጋር በቀጥታ በእጅ አዙር ደግሞ ከምዕራባዊያን ሀገራት ጋር ጦርነት ውስጥ ያለችው ሩሲያ ሉዓላዊነቴን የሚጋፋ ጥቃት ከተሰነዘረብኝ አልያም ከተሞከረ የኑክሌር ጦሬን ለመጠቀም እገደዳለሁ ማለቷ ይታወሳል።
አሜሪካ በበኩሏ ቻይና ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዳታደርግ ስታስጠነቅቅ ቻይና በበኩሏ የዩክሬን ጦርነትን በድርድር ለመፍታት እየሰራች መሆኗን ገልጻለች።