የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በሞቃዲሾ የሽብር ጥቃት የተጎዱትን ሰዎች ለማከም ዓለም አቀፍ ትብብር ጠየቁ
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ የተጎዱትን ለማከም እና ለተጎጂዎች እርዳታ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ ብሏል
በሽብር ጥቃቱ ቢያንስ 100 ሰዎች ሲገደሉ ከ300 ሰዎች በላይ ቆስለዋል
በሶማሊያ አልሻባብ ባደረሰው የአጥፍቶ መጥፋት አደጋ ቢያንስ 100 ዜጎች መገደላቸውን ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ተናግረዋል፡፡
በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል “በእናቶቻቸው እቅፍ ላይ የነበሩ ሕጻናት ይገኙበታል” ስለመባሉም ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
በተጨማሪም በሽብር ጥቃቱ 300 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተብሏል፡፡
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ በጥቃቱ የተጎዱትን ሰዎችን ለማከም ዓለም አቀፍ ትብብርን ጠይቀዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሓኖም ለፕሬዝዳንቱ ጥሪ ምላሽ ሰጥቷል።
በንጹሃን ላይ በደረሰው ጉዳት እጅጉን ማዘናቸው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ “የዓለም ጤና ድርጅት የተጎዱትን ለማከም እና ለተጎጂዎች እርዳታ በመስጠት መንግስትን ለማገዝ ዝግጁ ነው” ሲሉ ለሶማሊያ መንግስት ያላቸውን አጋርነት በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ አረጋግጠዋል፡፡
በሌላ በኩል አሜሪካ በሞቃዲሾ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት አውግዛለች፡፡
የዋይት ሀውስ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን “አሜሪካ በሞቃዲሾ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት አጥብቃ ታወግዛለች”ብለዋል፡፡
አሜሪካ የሶማሊያን ፌዴራላዊ መንግስት መሰል አስከፊ የሽብር ድርጊቶችን ለመከላከል በሚያደርገው ትግል ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ናት ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አልሻባብ በሁለት ቦታዎች በተሸከርካሪ ላይ የተጠመደ ቦምብ ያደረሰው የሽብር ጥቃት ህዝብ የሚሰበሰብባቸውን ቦታዎች ኢላማ ያደረገ ነው፡፡
አምቡላንስ የተጎዱ ሰዎችን በማንሳት ላይ እያለ በደረሰበት ሁለተኛው የአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ከነአሽከርካሪው ወድሟል የተባለ ሲሆን የትምህር ሚኒስቴር ህንጻ እና በአካባቢው የገንዘብ ምንዛሬ የፈጽሙ የነበሩ ሰዎች በአደጋው መጎዳታቸው ተገልጿል፡፡
ሶማሊያ በአልሻባብ የሽብር ቡድን መጠቃት ከጀመረች 20 ዓመት ያለፋት ሲሆን ጠንካራ የፌደራል መንግስት ተመስርቶ ሰላማዊ ሶማሊያን ለመፍጠር የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እና ተቋማት ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያም በአፍሪካ ህብረት ስር ላለው ሰላም አስከባሪ ሀይል ጦር ካዋጡ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን የሶማሊያ መንግስት በአልሻባብ ላይ የተጠናከረ ጥቃት ከከፈተ ወራቶች ተቆጥረዋል፡፡