የቭላዲቮስቶክ ዲስትሪክት ፍርድ ቤት የሩሲያዊ ዜጋ ንብረት በመስረቅ ጉዳት ያደረሰውን ብላክ እስከ ሐምሌ ድርስ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግበት ወስኗል
ሩሲያ ውስጥ በስርቆት ወንጀል የተከሰሰው ጎርደን ብላክ የተባለው የአሜሪካ ወታደር ከባድ ጉዳት ማድረሱን የሩሲያ ፍርድ ቤት ገልጿል።
ፔንታጎን ያለእውቅና ወደ ሩሲያ ሄዷል ያለው የብላክ እስር ዜጎቿ ወደ ሩሲያ እንዳይሄዱ ስታስጠነቀቅ ለነበረችው ተጨማሪ ራስምታት ሆኗል።
ወታደሩ በሩሲያዋ የሩቅ ምሰራቅ የወደብ ከተማ ቭላዲቮስቶክ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛል።
የቭላዲቮስቶክ ዲስትሪክት ፍርድ ቤት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የሩሲያዊ ዜጋ ንብረት በመስረቅ ጉዳት ያደረሰውን ብላክ እስከ ሐምሌ ድርስ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግበት ወስኗል።
ፍርድ ቤቱ ቁጥጥር እንዲደረግበት የወሰነው ብላክ በቅደመ ምርመራ ወቅት ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርስ ወይም እንዳያመልጥ ለማድረግ ነው ብሏል።
ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል ወታደሩ ጎርደን ብላክ እንደሚባል ይፋ አድርጓል።
መቀመጫውን ደቡብ ኮሪያ አድርጎ የነበረው ይህ ወታደር በሩሲያ የሩቅ ምስራቋ የወደብ ከተማ ቭላድቮስቶክ ከምትኖር ሩሲያዊት ሴት ጋር በኢንተርኔት አማካኝነት ተዋውቋል።
ይህን ተከትሎ ሁለቱ በደቡብ ኮሪያ ይገናኛሉ። አሜሪካዊው እሷን ለማግኘት ቭላዲቮስቶክ ከመጣ በኋላ በሁለቱ መካከል አለመግባባት ሲፈጠር ገንዘብ እንደሰረቃት በመግለጽ ለፖሊስ አመለከተች።
ወታደሩም ለመመለስ በአንድ ሆቴል ውስጥ ቲኬት እየገዛ በነበረበት ወቅት ፖሊስ በቁጥጥር ስር ሊያውለው ችሏል።
ፔንታጎን ወታደሩ ወደ ሩሲያ ያልፈቃድ በመግባት የጦሩን ህግ ጥሷል ብሏል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ሞስኮ የዋል ስትሪት ጋዜጠኛውን ኢቫን ገርሽኮቪችን ጨምሮ በርካታ አሜሪካውያንን እንድትለቅ እያግባቡ ነው።
ባለፈው አመት በፌደራል ሴኩሪቲ ሰርቪስ የታሰረው የ32 አመቱ ገርሽኮቪች፣ ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ በሰላይነት ተጠጥሮ ሩሲያ ውስጥ የታሰረ የመጀመሪያው አሜሪካ ጋዜጠኛ ሆኗል።
ጋዜጠኛው፣ የሚሰራበት ጋዜጣ እና አሜሪካ ሰላይ ነው የሚለውን ክስ አይቀበሉትም።