ትራምፕ ለዩክሬን ድጋፍ ለማቋረጥ የሚያሳልፉት ውሳኔ "ለኬቭ ጦር የሞት ቅጣት ነው" - ሩሲያ
ተመራጩ ፕሬዝዳንት የዩክሬኑን ጦርነት የሚያስቆም እቅድ ያቀረቡላቸውን ጡረተኛ ጀነራል ኬት ኬሎግ የሩሲያና ዩክሬን ልዩ መልዕክተኛ አድርገው መርጠዋል
የባይደን አስተዳደር ከየካቲት 2022 ወዲህ ለዩክሬን ከ64 ቢሊየን ዶላር በላይ ወታደራዊ ድጋፍ አድርጓል
ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ ለማቋረጥ የሚያሳልፉት የትኛውም ውሳኔ "ለዩክሬን ጦር የሞት ቅጣት ነው" አሉ በተመድ የሩሲያ ምክትል አምባደር ዲሚትሪ ፖሊያንስኪ።
የጸጥታው ምክርቤት ትናንት ባደረገው ስብሰባ ንግግር ያደረጉት ፖሊያንስኪ፥ የባይደን አስተዳደር ለኬቭ ወታደራዊ ድጋፉን ማጠናከሩ "በሩሲያ እና ወደ ዋይትሃውስ በሚገባው አዲስ ቡድን ውስጥ ትርምስ ፈጥሯል" ነው ያሉት።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ የትራምፕ በጥር ወር ወደ ነጩ ቤተመንግስ መመለስ ያስደነገጣቸውም የድጋፉ ይቋረጣል ስጋት መሆኑን አብራርተዋል።
አምባሳደሩ የትራምፕ አስተዳደር በባይደን የስልጣን ዘመን ለዩክሬን የተደረጉ ድጋፎችን ኦዲት ያደርጋል ብለው እንደሚያምኑ መናገራቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
ኬቭ የሰሜን ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባላትን ከሩሲያ ጋር ቀጥተኛ ጦርነት ውስጥ እያስገባች ነው ሲሉ የወቀሱት ፖሊያንስኪ ስለሰጡት አስተያየት ከትራምፕ የሽግግር ቡድን እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም።
በምርጫ ቅስቀሳቸው የዩክሬኑን ጦርነት በአንድ ቀን አስቆማለሁ ያሉት ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል ነው የተባለ እቅድ ያቀረቡላቸውን ኬት ኬሎግ የሩሲያ እና ዩክሬን ልዩ መልዕክተኛ አድርገው ማጨታቸው ተዘግቧል።
የቀድሞው የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪና ጡረተኛው ጀነራል ኬሎግ ያቀረቡት እቅድ ሩሲያ እና ዩክሬን በሚዋጉበት ስፍራ ላይ እንዳሉ ጦርነቱ ቆሞ ወደ ድርድር እንዲገቡ ጫና መፍጠርን ያካተተ መሆኑን ሬውተርስ ሰኔ ወር ላይ ያወጣው ዘገባ አመላክቶ ነበር።
ይህም የዩክሬንን 20 በመቶ የሚጠጋ መሬት ለያዘችው ሞስኮ ትልቅ የመደራደር አቅምን የሚፈጥር ነው በሚል በኬቭ መተቸቱ የሚታወስ ነው።
ዩክሬን በጆ ባይደን አስተዳደር የስልጣን ዘመን ከፍተኛውን ድጋፍ ያገኘችው ከአሜሪካ ነው።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረበት የካቲት 2022 ጀምሮ ከ64 ቢሊየን ዶላር በላይ ወታደራዊ ድጋፍ ተደርጎላታል።
ይህ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ በአሜሪካ ምርጫ ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኖም ጦርነቱን በፍጥነት አስቁመው ድጋፉን እንደሚያቋርጡ ቃል የገቡት ትራምፕ ለድል እንዲበቁ አስተዋጽኦ ማድረጉ ይታወሳል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም በትራምፕ የተመረጡት ኬት ኬሎግ ኬቭ ከሞስኮ ጋር የሰላም ንግግር ካላደረገች ከዋሽንግተን ወታደራዊ ድጋፍ እንደማታገኝ ለፎክስ ኒውስ መናገራቸውም አይዘነጋም።