የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾይጉ ምክትሎች ከሆኑት አንዱ ጉቦ በመቀበል ተጠርጥረው ታስራዋል
የሩሲያው መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾይጉ ምክትሎች ከሆኑት አንዱ ጉቦ በመቀበል ተጠርጥረው ታሰሩ።
ምክትል ሚኒስትሩ ፕሬዝደንት ፑቲን በዩክሬን ልዩ ያሉትን ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈቱ ከየካቲት 2022 ወዲህ በሙስና ተጠርጥረው የታሰሩ ከፍተኛ ባለስልጣን መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትሩ ቲሙር ኢቫኖቭ በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው ማክሰኞ ነው።
ምክትል ሚኒስትሩ በተጠረጠሩበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የ15 አመታት እስር ይጠብቃቸዋል።
ፕሬዝደንት ፑቲን በዩክሬን ባለው ጦርነት ስራ ሰጥተዋቸው እየሰሩ የነበሩት የሾይጉ አጋር ድንገተኛ እስር፣ ሩሲያ ከሶቬት ህብረት መውደቅ በኋላ በጦሯ ውስጥ በተንሰራፋው ሙስና ላይ ልትዘምት ነው የሚል ጥርጣሬን ፈጥሯል።
ክሬሚሊን ፕሬዝደንት ፑቲን እና መከላከያ ሚኒስትሩ ሾይጉ የምክትል ሚኒስትሩ እስር ጉዳይ ተግሯቸዋል ብሏል። ኢቫኖቭ ከፍተኛ የመከላከያ ባለስጣናት ማክሰኞ እለት ባደረጉት ስብሰባ ላይ ተገኝተው ነበር።
ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ ምክትል ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ኢቫኖቭ በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ንብረት የማስተዳደር ኃላፊነት ነበራቸው።
ሮይተርስ የሩሲያውን ኮመርሳንት ጋዜጣ ጠቅሶ እንደዘገበዘው የ48ቱ ኢቫኖቭ በቁጥጥር ስር የዋሉት በሶቬት ጊዜ የነበረውን ኬጂቢን በተካው የሩሲያው ፌደራል ሴኩሪቲ ሰርቪስ(ኤፍኤስቢ) ነው።
ፕሬዝደንት ፑቲን ባለፈው ወር ነበር በመከላከያ ሚኒስትር ውስጥ ካሉ ግዥዎች ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ሙስናዎችን እንዲመነጥር ለኤፍኤስቢ የነገሩት።
ከምክትል ሚኒስትሩ ጋር ሌሎች የታሰሩት ሰዎች መኖራቸውን ዘገባው ጠቅሷል።