የሩሲያው የፊልም ስቱዲዮ “ሞስፊልም” ለሀገሪቱ ጦር 36 ታንኮች መስጠቱን ገለጸ
የፊልም ሰሪ ኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ በክሬምሊን ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር መክረዋል
በፈረንጆቹ 1924 የተቋቋመው “ሞስፊልም” ከ2 ሺህ 500 በላይ ፊልሞችና ዘጋቢ ፊልሞች ሰርቷል
የሩሲያው የፊል ስቱዲዮ “ሞስፊልም” ለሩሲያ ጦር 36 የሶቪየት ዘመን ታንኮች መስጠቱን አስታወቀ።
የስቱዲዮው ዋና ስራ አስፈጻሚ ካረን ሻክናዛሮቭ ትናንት ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር መክረዋል።
ለፊልም ስራ የሚውሉ በርካታ ታንኮችና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ያሉት “ሞስፊልም” ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በገባችበት ጦርነት ሊጠቅሙ ይችላሉ ያላቸውን ታንኮች ማበርከቱን ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
የፊልም ኩባንያው 28 “ቲ-55” መካከለኛ ታንኮች፣ ስምንት “ፒቲ-76” ታንኮች እና ስምንት ጥይት የማይበሳቸው ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ለሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ማስረከቡን ነው የገለጸው።
“ሞስፊልም” በዩክሬን ለሚካሄደው ጦርነት የሚውል 6 ሚሊየን ሩብል (61 ሺህ ዶላር) ድጋፍ በማድረግም አጋርነቱን ማሳየቱን ዋና ስራ አስፈጻሚው ለፑቲን እንደነገሯቸው የሩሲያው አርቲ ዘግቧል።
ከአራት ወራት በኋላ ሶስተኛ አመቱን የሚይዘው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በርካታ ታንኮችን አውድሟል።
አለማቀፉ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ባለፈው አመት የካቲት ወር ባወጣው ሪፖርት ሩሲያ በዩክሬን ከ3 ሺህ በላይ ታንኮቿ መውደማቸውን ገልጾ ነበር። ሌሎች ተቋማት እና መገናኛ ብዙሃን ደግሞ አሃዙን እስከ 8 ሺህ ያደርሱታል።
ሞስኮ የደረሰባት ኪሳራ የሶቪየት ዘመን ታንኮችን በፍጥነት በማደስ ወደ ዩክሬን ለማስገባት እንዳስገደዳት ሲገለጽ ቆይቷል።
ዩክሬንም በተመሳሳይ በርካታ ታንኮችን በጦርነቱ ብታጣም ከምዕራባውያን የተደረገላት ድጋፍ በመጠኑም ቢሆን የሩሲያን ጥቃት እንድትከላከል አስችሏታል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
በፈረንጆቹ በ1924 የተቋቋመው የሩሲያው ግዙፍ የፊልም ስቱዲዮ “ሞስፊልም” ለሩሲያ ጦር ያበረከታቸው ታንኮች ወደ ዩክሬን ስለመግባታቸው አልታወቀም።
ሞስኮ ታይምስ ሩሲያ ከዚህ ቀደም የሶቪየት ዘመን ታንኮችን ወደ ዩክሬን ማስገባቷን የሚያመላክቱ ዘገባዎች መውጣታቸውን አስታውሷል።
የ100 አመት ባለጸጋው “ሞስፊልም” ከ2 ሺህ 500 በላይ ፊልሞችና ዘጋቢ ፊልሞች ሰርቷል። ከእነዚህም መካከል በ1968 እና 1980 በውጭ ሀገር ቋንቋ በተሰሩ ፊልሞች ዘርፍ ኦስካር ያሸነፉት “ዋር ኤንድ ፒስ” እና “ሞስኮ ኖት ቢሊቭ ኢን ቲርስ” ተጠቃሽ ናቸው።