የሩስያ ኤምባሲ ድርጊቱን "አሳዛኝ" ሲል ገልጿል
በአውስትራሊያ "ኦፕን ቴኒስ" ውድድር ወቅት የሩስያ እና የቤላሩስ ባንዲራዎች እንዳይታዩ ታገደ።
በአውስትራሊያ እና በኒውዚላንድ የዩክሬን አምባሳደር ቫሲል ማይሮሽኒቼንኮ የሩስያ ባንዲራ በቴነስ ሜዳው ተንጠልጥሎ ከሀገራቸው ተጨዋች ካትሪና ባይንድል ጋር የሚያሳይ ፎቶግራፍ አጋርተዋል።
"አምባሳደሩ የሩሲያ ባንዲራ በአደባባይ መታየቱን አጥብቄ አወግዛለሁ" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
"ቴኒስ አውስትራሊያ 'የገለልተኛ ባንዲራ' ፖሊሲውን በአስቸኳይ እንዲያስፈጽም ጥሪ አቀርባለሁ" ሲሉም አክለዋል።
ቴኒስ አውስትራሊያ የሁለቱን ሀገራት ባንዲራ በማገድ ምላሽ ሰጥቷል።
በሰጠው መግለጫም "በአውስትራሊያ ኦፕን በውድድር ሜዳው አካባቢ የሩሲያ እና ቤላሩስ ባንዲራዎች ተከልክለዋል" ብሏል።
"የእኛ ፖሊሲ ደጋፊዎቹ ባንዲራዎች እንዲያስገቡ ይፈቅዳል ፤ ነገር ግን እነሱን ተጠቅሞ ረብሻ መፍጠር አይችልም፤ ይሁን እንጂ ባንዲራ ወደ ውድድር ሜዳው የማስገባት ክስተት አጋጥሞናል" ብሏል።
እገዳው ወዲያውኑ ተግባራዊ ይሆናል መባሉንም ሬውተርስ ዘግቧል።
ቴኒስ አውስትራሊያ "ከተጫዋቾቹ እና ከደጋፊዎቻችን ጋር በቴኒስ ለመደሰት የምንችለውን ምቹ ሁኔታ ለማረጋገጥ መስራታችንን እንቀጥላለን" ብሏል።
ሞስኮ “ልዩ ተልዕኮ” በምትለው የዩክሬን ጦርነት ሩሲያ ቤላሩስን እንደ ቁልፍ መነሻ ቦታ እየተጠቀመች ነው በሚል በኬቭ ትወቀሳለች።
የሩሲያ እና የቤላሩስ ተጫዋቾች ባለፈው ዓመት ከትልቁ የቴኒስ ውድድር ዊምብልደን ታግደው ነበር። ነገር ግን በአውስትራሊያ ኦፕን ላይ ያለ ብሄራዊ ቡድን እንደ ግለሰብ አትሌቶች መወዳደር ችለዋል ነው የተባለው።
ተጨዋቾቹ እንደሌሎች ተጫዋቾች በቴሌቭዥን ስርጭቶች ላይ ባንዲራ ከስማቸው ጎን አይታይም ተብሏል።
በአውስትራሊያ የሚገኘው የሩስያ ኤምባሲ ቴኒስ አውስትራሊያ ለፖለቲካዊ መጠቀሚያነት እጁን ሰጥቷል ብሏል።