ሩሲያ በሞስኮ የሚገኙትን የጀርመን አምባሳደር ለማብራሪያ ጠራች
የጀርመን ወታደሮች ለዩክሬን ስለሚደረግ ሚስጢራዊ ድጋፍ ሲያወሩ የተቀዳው ድምጽ በሩሲያ መጠለፉን ተከትሎ ነው አምባሳደሩ የተጠሩት
የሩሲያ ቀዳሚዋ የነዳጅ ገዥ ሀገር ጀርመን በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከሞስኮ ጋር ግንኙነቷ ሻክሯል
ሩሲያ በሞስኮ የሚገኙትን የጀርመን አምባሳደር ለማብራሪያ ጠራች።
አምባሳደር አሌክሳንደር ላምብስዶርፍ ለማብራሪያ የተጠሩት የጀርመን ወታደሮች ለዩክሬን ሊደረግ ስለሚችል ድጋፍ በሚስጢር ያወሩበት የድምጽ ቅጂ በሞስኮ እጅ መግባቱን ተከትሎ ነው።
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሹልዝ ባለፈው ሳምንት ሀገራቸውም ሆነች የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ወታደሮችን ወደ ዩክሬን የመላክ እቅድ እንደሌላቸው መነገራቸው ይታወሳል።
መራሄ መንግስቱ ወታደሮችን መላክ ከሩሲያ ጋር በቀጥታ ጦርነት ውስጥ ያስገባናል የሚል መግለጫ በሰጡበት እለት ግን ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖቻቸው በክሬሚያ ድልድይ ላይ ሊደረግ ስለሚችል ጥቃት እየመከሩ ነበር ብሏል አርቲ በዘገባው።
የጀርመን አየር ሃይል አመራሮችን ጨምሮ ወታደሮች በሚስጢር ሲነጋገሩ የተቀዳው ድምጽም በሩሲይ የተጠለፈ ሲሆን፥ ሞስኮ የጀርመኑ አምባሳደር በጉዳዩ ላይ ማብራሪያን እንዲሰጡ ጠርታቸዋለች።
በርሊን ሚስጢራዊው ንግግር በሩሲያ መጠለፉን ብታረጋግጥም እስካሁን የድምጽ ቅጂው ምን ይዘት እንዳለው መግለጫ አላወጣችም።
በድምጽ ቅጂው የጀርመን ወታደሮች ታውረስ የተሰኘውን ክሩዝ ሚሳኤል ለኬቭ በመላክ የክሬሚያ ድልድይን እንድታፈራርሰው እናግዛት፤ ለዩክሬን በሚስጢር መረጃ እንስጣት የሚሉና ሌሎች ሃሳቦችን ሲለዋወጡ ይደመጣል ብሏል የሩሲያው የዜና ወኪል ታስ።
ሚስጢራዊው ንግግር ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገው ጦርነት ከኬቭ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሚያግዟት ምዕራባውያን ጋር መሆኑን ማሳያ አድርጋ አቅርባዋለች።
የጀርመን ፖለቲከኞችም ጀርመን ለዩክሬን ታውረስ የተሰኘውን ሚሳኤል ለዩክሬን እንዳትሰጥ ጫና እያደረጉ መሆኑን ሬውተርስ ዘግቧል።
የሩሲያ ቀዳሚዋ የነዳጅ ገዥ ሀገር ጀርመን ከዩክሬን ጦርነት መጀመር ወዲህ ከሞስኮ ጋር ግንኙነቷ ሻክሯል።
በርሊን ለኬቭ ሊዮፓርድ 2 ታንኮችን ለመስጠት መስማማቷ የቭላድሚር ፑቲንን ሀገር እጅግ ማስቆጣቱ የሚታወስ ነው።
ሀገራቱ በተደጋጋሚ ዲፕሎማቶችን ከሀገራቸው በማስወጣትም ኩርፊያቸውን ሲገልጡ መቆየታቸው አይዘነጋም።