የአፍሪካ ሕብረት በጦርነት ላይ ያሉ ወገኖችን ለማስታረቅ የሚያደርገውን ጥረት ሩሲያ በመልካም ጎን እንምትመለከተው አስታውቃለች
የአፍሪካ ሕብረት እና ሩሲያ በኢትዮጵያ ባለው ወቅታዊ ሁኔታላይ መወያየታቸው ተነግሯል።
ሁለቱ ወገኖች ውይይት ያደረጉት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በሞስኮ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት መሆኑም ተገልጿል።
ሙሳ ፋኪ ማሃማት በሞስኮ ቆይታቸው ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል። ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ ያው ከባድ ችግር ፈጣን መፍትሄ እንደሚፈልግም ተነጋግረዋል ነው የተባለው።
የአፍሪካ ሕብረት በጦርነት ላይ ያሉ ወገኖችን ለማስታረቅ እያደረገ ያለውን ጥረት ሩሲያ በመልካም ጎን እንምትመለከተው መገለጹን አል ዐይን ኒውስ በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከዚህ ባለፈም በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ያሉ ግጭቶችን መፍታት እንደሚገባ ሁለቱ ወገኖች ተግባብተዋል ነው የተባለው። ከዚህ ባለፈም በሊቢያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እና በሌሎች ሀገራት ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ውይይት ተደርጓል ነው የተባለው።
ሙሳ ፋኪ ማሃማትና ሰርጌ ላቭሮቭ ከ አውሮፓውያኑ 2022 እስከ 2025 በሁለቱ ወገኖች የሚተገበር የትብብር ስራን ቶሎ ለማጠናቀቅም ተስማምተዋል ተብሏል። ይህ የትብብር ስራ በሩሲያዋ የሶቺ ከተማ የተፈረመው የሁለቱ ወገኖች ትብብር አካል እንደሆነም ተገልጿል።
ሁለቱ ወገኖች በሩሲያ እና በአፍሪካ ሕብረት ስትራቴጂያዊ ወዳጅነት ዙሪያም መወያየታቸው የተገለጸ ሲሆን ውይይታቸውም የጋራ ግቦችን ስለማሳካት፤ ሰላምን ስለማስፈን፤ ጸጥታን ለማረጋገጥ፤ መረጋጋትን በማምጣት ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ዙሪያ ላይ ያተኮረ እንደነበርም ተገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያለውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ምክክር ተደርጓል ነው የተባለው።
ሽብርተኝነትን በጋራ መመከትን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ስጋቶችን መቅረፍ፤ ኢኮኖሚያዊ ትስስሮችን ማበረታታት፤ በትምህርት፣በሳይንስ እና በቴክኖሎጅ በጋራ መስራትና የመሳሰሉት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ተነጋግረዋል ነው የተባለው።
በአጠቃላይ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሻ ፋኪማሃማት ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ አጀንዳዎች ላይ መክረዋል ነው የተባለው።