የኢትዮጵያ ግዛት አንድነት የግድ መከበር እንዳለበትም ሩሲያ አሳስባለች
በኢትዮጵያ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ሩሲያ በድጋሚ ጠየቀች።
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛራኮቫ በሳምንታዊ መግለጫቸው ላይ ኢትዮጵያን በሚመለከት እንዳሉት ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ሩሲያ የኢትዮጵያን ጉዳይ እየተከታተለች እንደሆነ የተናገሩት ቃል አቀባይዋ ሰሞኑን በደሴ እና በኮምቦልቻ ከተሞች የተካሄዱት ጦርነቶች የሲቪል ዜጎችን ህይወት መጉዳቱን አክለዋል።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ የበላይነት ለማገኘት እየታገሉ ያሉ ወገኖች ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሁሉም አካላት ፖለቲካዊ ፍላጎት ሊኖራቸው እንደሚገባም ማሪያ ዛራኮቫ ተናግረዋል።
ሩሲያ የኢትዮጵያን ግዛት አንድነት መከበር ለድርድር የማይቀርብ እና ግጭቱን መፈቻ መንገድ ሊሆን እንደማይችል ታምናለችም ብለዋል ቃል አቀባየዋ።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ግጭቱን ለማስቆም ኢትዮጵያውያን እንዲወያዩ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
ኬንያታ የኢትዮጵያ ተፋላሚ ወገኖች ድርድር ይጀምሩ ሲሉ ነው የጠየቁት።
ህወሓት እና ኦነግ ሸኔ የፌደራል መንግስቱን ለመውጋት ቅንጅት መፍጠራቸው ጦርነቱ ሌላ መልክ እንዲኖረው እና እንዲራዘም እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
በፌደራል መንግስቱ እና በህወሃት መካከል እስካሁን ትርጉም ያለው ድርድር አለመጀመሩ ጦርነቱ ከአንድ ዓመት በላይ እንዲቀጥል አድርጎታልም ነው ኡሁሩ ያሉት።
የኢትዮጵያ ሁኔታ እንዳሳሰባቸው የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ጦርነቱን ለማስቆም ድርድር እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ኬንያን ጨምሮ አፍሪካ እና ዓለም ሰላማዊ ኢትዮጵያን ማየት ይፈልጋል ያሉም ሲሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተመካክሮ ለአገሩ ሰላም መፍትሄ እንዲፈልግ አሳስበዋል።