አሜሪካና አጋሮቿ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫቸውን ከአዲስ አበባ ወደ ሌላ ቦታ እንዲያዘዋውሩ እየወተወቱ ነው- መንግስት
የአሜሪካ ኤምባሲ እና አንድአንድ የአሜሪካ መንግስት ተወካዮች በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለው ጫና “አሳፋሪ” በሆነ መንገድ መቀጠሉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ ዛሬ ረፋድ ላይ በሰጡት መግለጫ፤ አሜሪካ ከአንድ ሳመንት በፊት የህወሓት ታጣቂዎች አዲስ አበባን ከበዋል የሚል ፕሮፖጋዳ በመንዛት ዜጎቿ ከሀገር እንዲወጡ እና ሌሎች ኤምባሲዎችም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ጫና ስትፈጥር ነበር ብለዋል።
ይህ አልሳካ ሲላቸው ሌላ አጀንዳ ይዘው ቀርበዋል ያሉት አቶ ከበደ፤ “በትናትናው እለት ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ የሽበር ጥቃት ሊፈፀም ይችላል የሚል ሽበር የሚፈጥር መግለጫ አውጥተዋል” ሲሉም ተናግረዋል።
“እንዲህ አይነት መግለጫዎች ከእውነት የራቁ እና ሽበር ለመፍጠር የተሸረቡ መሆኑን በመግለፅ፤ “ለህወሓት የወገነ ግልጽ ጦርነት መከፈቱን የሚያረጋግጥ ነው” ብለዋል ሚኒስትር ደኤታው።
“ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ከዚህ ቀደም የሽበር ስጋት ሲኖር መረጃ ይለዋወጡ ነበር፤ አሁን ግን የአሜሪካ ኤምሳቢ ምንም በሌለበት ያወጣው መግለጫ የኢትዮጵያን ገጽታ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ለማጠልሸት የተሰራ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
እንዲህ አይነት ተግባራት የዲፕሎማሲያዊ ህጎች እና ልማዶችን የሚጥሱ ናቸው ያሉት አቶ ከበደ፤ የሁለቱን ሀገራት የቆየ እና ታሪካዊ ግንኙነት የሚያበላሽ መሆኑንም ገልጸዋል።
ስለዚህም የአሜሪካ መንግስትም ይሁን መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የአሜሪካ ኤምባሲ ሽብርን ከሚዛ እና ኃላፊነት ከጎደለው ተግባራቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
ሚኒሰትር ደኤታው አክለውም፤ የአሜሪካ ኤምባሲ ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመሆንም መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ወደ ሌላ ሀገር እንዲዘዋወሩ ጫናዎችን እየፈጠሩ እንደሆነም አስታውቀዋል።
ይህንን ለማሳካትም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ በተለይም ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ቅሬታ ያላቸው ሀገራት በማስተባበር እየሰራች መሆኗንም ያነሱ ሲሆን፤ ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
መሰረታቸውን አሜሪካ ያደረጉ የረድኤት ድርጅቶች “ከኢትዮጵያ እንወጣለን፤ ከዚህ በኋላ ሰብዓዊ ድጋፍ አናደርግም የሚሉ ማስፈራሪያዎችን ሲያሰሙ ቆይተዋልም” ብለዋል።
“ኢትዮጵያውያን ለስንዴ ብለን ሉአላዊነታችንን የማናስደፍር ህዝቦች መሆናችንን በአንድነት ሆነን ይህንን ጊዜ በማሳለፍ እናሳያለን” ያሉት አቶ ከበደ “አፍሪካዊያን ትብብራቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል።