የሩሲያ ላዳ መኪኖችን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማምረት ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ
የላዳ መኪና አምራች ኩባንያ የሆነው አቭቶቫዝ ከኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል
ሩሲያ ሰራሽ የላዳ ታክሲዎች በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ከገቡ ከ50 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል
የሩሲያ ላዳ መኪኖችን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማምረት ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ፡፡
ከፈረንጆቹ 1970ዎቹ ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ የገቡት ሩሲያ ሰራሽ ታክሲዎች ቀስ በቀስ አዲስ ምርቶች ወደ አፍሪካ መግባት ትተው ቆይተዋል፡፡
ከሶቭየት ህብረት መከፋፈል በኋላ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ ገበያ እየራቁ የነበሩት የላዳ ታክሲዎች ዳግም በአዲስ ምርት እና ዲዛይን ገበያውን ሊቀላቀሉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቨግኒ ተረኪን እንዳሉት ላዳ ታክሲዎች በኢትዮጵያ ማምረት የሚያስችሉ ስምምነቶች መፈረሙን ተከትሎ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡
አምባሳደር ተረኪን ከሩሲያው ሪያ ኖቮስቲ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ “ላዳ ታክሲዎችን በኢትዮጵያ ማምረት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው፣ ላዳ በኢትዮጵያ የታወቀ መሆኑ ታክሲዎቹን ዳግም በዚሁ ለማምረት አስመርጧታል“ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ የላዳ ተሽከርካሪን ምርት ወደ አፍሪካ ልትመልስ መሆኗን ገለጸች
የላዳ መኪኖች አምራች የሆነው አቭቶቫዝ ኩባንያ ባሳለፍነው ዓመት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በኢንዱሰትሪ ፓርኮች እና ሀገር በቀል ድርጅቶችን ጎብኝተው ተመልሰዋል፡፡
ኩባንያው ከቀድሞው ሜቴክ ወይም ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ላዳ መኪኖቹን ለማምረት ስምምነት መፈራረሙ አይዘነጋም፡፡
ድርጅቱ ከዚህ በፊት በሰጠው መግለጫ የላዳ መኪኖችን በኢትዮጵያ በማምረት ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የመላክ እቅድ መንደፉንም አስታውቆም ነበር፡፡