ሩሲያ የምትመካባቸውና “የሚሳይሎች ዲዛይነር” በመባል የሚታወቁት ፓቬል ካሜኔቭ በ86 ዓመታቸው አረፉ
የ"ካሊበር" ሚሳይሎች በአሁኑ የዩክሬን ጦርነት ጥቅም ላይ ውለው ዩክሬናውያንን ያስደነገጡ የጦር መሳሪያዎች ናቸው
ፓቬል ካሜኔቭ ፤ የተራቀቁ የሚሳኤል ስርዓቶችን በማምረት የተሳተፉ ድንቅ ሩሲያዊ የሮኬት ሳይንቲስት ናቸው
ሩሲያ የምትመካባቸውና “የሚሳይሎች ዲዛይነር” በመባል የሚታወቁት ፓቬል ካሜኔቭ በ86 ዓመታቸው አረፉ፡፡
በሩሲያ የመከላከያ ኢንዱስትሪዎች ስማቸው በቀዳሚነት ከሚነሳ የሚሳይል ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት ካሜኔቭ በተለይም ክንፍ ያላቸው "ካሊበር" ሚሳይሎች ዲዛይን በማድረግና በማምረቱ ሂደት ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸው ይነገርላቸዋል፡፡
እንደ አንድ ወታደራዊ ባለሙያዎች ገለጻ ከሆነ "ካሊበር" ሚሳይል በጣም አስፈላጊ እና ገዳይ ከሆኑት የሩሲያ የጦር መሳሪያዎች አንዱ ነው፡፡
“አልማስ-አንቴይ” የተሰኘው የሩሲያ ኩባንያ ባወጣው መግለጫ ካሜኔቭ ብዙ የተራቀቁ የሚሳኤል ስርዓቶችን በማምረት የተሳተፉ ሩሲያዊ መሆናቸው ገልጿል፡፡
በአሁኑ የዩክሬን ጦርነት ጥቅም ላይ እየዋሉ ካሉ በደርዘን የሚቆጠሩ የሚሳይል ጦር መሳሪያዎችን ከማዘመን እና ከማምረት ጋር የተያያዙ በርካታ ፕሮጀክቶችን ጀርባ እሳቸው (ፓቬል ካሜኔቭ ) ነበሩም ብሏል ኩባኒያው፡፡
በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ሩሲያ የረዥም ርቀት የአየር ድብደባዎችን ስትጠቀም "ካሊበር" ሚሳይሎች ዩክሬናውያንን ካስደነገጡ የጦር መሳሪያዎች እንደነበሩ በመጥቀስ፡፡
መግለጫው ካሜኔቭ እንደፈረንጆቹ በ 1996 የ "ኖቫተር" ዲዛይን ቢሮ የማስተዳደር ኃላፊነት መረከባቸውንና እስከ 2017 ድረስ የተቋሙ ዳይሬክተር በመሆን ኃለፊነታቸውን በከፍተኛ ብቃት የተወጡ ሰው ነበሩ ሲልም አትቷል፡፡
ከ "ካሊበር" ሚሳይሎች በተጨማሪ "ኢስካንደር" ሚሳይል ስርዓት የሚጠቀሙባቸው መካከለኛ ርቀት ሚሳይሎች የተሰሩት በእሳቸው የመሪነት ዘመን እንደነበረም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ካሜኔቭ በ 2017 የ "አልማስ" ኩባንያ ሳይንሳዊ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ሆነው ለሀገራቸው ዘመን የማይሸረው ተግባር ፈጽመው ያለፉ የሩሲያ ጀግና መሆናቸውም በርካቶች ይመሰክራሉ፡፡