ግዙፉ የሩሲያ የኒውክሌር ኩባንያ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስምምነት መፈጸሙ ተገለጸ
ሮሳቶም የተባለው ኩባንያው የኒውክሌር ሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ማዕከል መግንባትን ያካተተ ስምምነት ነው የፈጸመው
በስምምነቱ መሰረት ለሰላማዊ አላማ የሚውሉ የሀይል አማራጮችን ለማስተዋወቅ የምርምር ስራዎች ይደረጋሉ ተብሏል
ግፉ የሩሲያ የኒውክሌር ኩባንያ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በኒውክሌር ሳይንስ ልማት ስምምነት መፈጸሙ ተነግሯል፡፡
ሮሳቶም የተባለው ኩባንያ በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር የኒውክሌር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ለመገንባት የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት ለማካሄድ ከኢትዮጵያ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት መፈጸሙን የሩሲያው አርቲ አስነብቧል፡፡
ኩባንያው በቅርቡ የኑክሌር እና የጨረር ቴክኖሎጂ ከሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ጋር እንዴት መጣጣም እንደሚችል ለማወቅ የኢትዮጵያን ኢነርጂ ዘርፍ መገምገም እንደሚጀምር የሩስያ አቶሚክ ኢነርጂ ባለስልጣን ያወጣው መረጃ አመላክቷል፡፡
የዚህ ግምገማ ውጤት በኑክሌር ሀይል አቅም ላይ የተመሰረተ ለንግድ ምርቶች እና አገልግሎቶች ገበያ መሰረት በመጣል የቴክኖሎጂዎቹ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ የገበያ እድሎችን ለመለየት ያስችላል ነው የተባለው፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የኑክሌር ሀይል አቅምን እንድታሳድግ ሮሳቶም የሚኖረውን ሚና በመግለጽ በስምምነቱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
የሮሳቶም ዋና ዳይሬክተር ኢሊያ ቬርጊዛቭ ኩባንያው በአፍሪካ አህጉር ላይ የኒውክሌር ልማትን ለማጎልበት ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸው፣ "በአፍሪካ አህጉር ላይ የኒውክሌር እና የጨረር ቴክኖሎጂዎችን ለማዳበር በተለያዩ ፕሮጀክቶች እና የጋራ መፍትሄዎች ላይ ከአለም አቀፍ አጋሮቻችን ጋር እየሰራን ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ዳይሬክተር አናቶሊ ባሽኪን በበኩላቸው በአፍሪካ ያለውን የሀይል ፍላጎት ለማሟላት እንዲሁም እያደጉ ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የሀይል አቅርቦት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሞስኮ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአህጉሪቷ ሌሎች ሀገራት ጋር በቅርበት መስራቷን ትቀጥላለች ነው ያሉት፡፡
ይህ ሂደትም ሰላማዊ የኒውክሌር ሀይል አጠቃቀም ፕሮጀክቶችን ማስተዋወቅ አላማ ያላቸው ሁለገብ የምርምር ስራዎችን እና የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች ላይ የተመሰረቱ ማዕከሎችን መገንባት ያካትታሉ ተብሏል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ቡርኪናፋሶ በሴንት ፒተርስበርግ ሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ መሪዋ ኢብራሂም ትራኦሬ ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ ከሮሳቶም ጋር የኒውክሌር ሃይል ማመንጫ ለመገንባት ስምምነት ተፈራርማለች።