በሩሲያ ከራዳር ተሰውራ የጠፋችው አውሮፕላን ተገኘች፤ተሳፋሪዎቹም በህይወት ተርፈዋል
በሩስያ አውሮፕላን ከራዳር ግንኙነት ውጭ ሆና ስትጠፋ በዚህ ወር ለሁለተኛ ጊዜ ነው
የሩሲያ ባለስልጣናት የጠፋችውን አውሮፕላን ለመፈለግ ሁለት ሄሊኮፕተሮች ማሰማራታቸውን ገልጸው ነበር
በሩሲያ 19 ሰዎችን አሳፍራ የነበረችውና ከራዳር እይታ ውጭ የሆነችው ኤኤን-28 አውሮፕላን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አርፋለች፤ ተሳፋሪዎቹም በህይወት ተርፈዋል፡፡
ኤኤን-28/ An-28 የተሰኘች አንቶኖቭ አውፕላን ከራዳር ውጭ በመሆን ሳይቤሪያ ቶምስክ ግዛት እንደተሰወረች የግዛቱ ባለስልጣናት ገልጸው ነበር፡፡
የግዘቱ አስተዳዳሪ ሰርጌይ ዜቫችኪን እንዳሉት ከሆነ የጠፋችውን አውሮፕላን ለመፈለግ ሁለት ሄሊኮፕተሮች እንዲሰማሩ ተደርገዋል፡፡ ሲላ /SiLA/ የተባለውን በሳይቤሪያ አየር ክልል የሚንቀሳቀስ አየር መንገድ ንብረት የሆነችው አውሮፕላኗ፤ በውስጧ ከነበሩ 17 መንገደኞች በተጨማሪ 3 የአውሮፕላኗ ሰራተኞች እንደነበሩ አስተዳዳሪው አስታውቀዋል፡፡
በሩስያ አውሮፕላን ከራዳር ውጭ ሆና ስትጠፋ በዚህ ወር ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑንም ነው ሮይተርስ ዘገቧል፡፡
ከሁለት ሳምነታት በፊት An-26 የተሰኘች አውሮፕላን ከእይታ ውጭ ተሰውራ በሩስያ ሩቅ ምስራቅ አቅጣጫ በሚገኝ ካምቻትካ ግዛት ውስጥ ተከስክሳ የ28 ሰዎች ህይወት ማለፉ የሚታወስ ነው፡፡
እንደፈረንጆቹ 2012 An-28 የተሰኘች ተመሳሳይ አውሮፕላን በካምቻታካ ደኖች ወድቃ 10 ሰዎች መሞታቸውንም እንዲሁ የሚታወስ ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሩሲያ የአቪዬሽን ደህንነት ደረጃዎች እየተሻሻለ መምጣቱ ቢነገረም አልፎ አልፎ መሰል አደጋዎች ማጋጠሙ አልቀረም፡፡