ሩሲያ “ሳርማት” አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳዔል በብዛት ማምረት ጀመረች
ፑቲን ሩሲያ “ሳርማት” አህጉር አቋራጭ ሚሳዔልን በዓመቱ መጨረሻ ለውጊያ እንደምታሰማራ አስታውቀዋል
“ሳርማት” 15 የኒኩሌር አረሮችን የሚሸከም ሲሆን፤ እስከ 35 ሺህ ኪ.ሜ ርቀት ማጥቃት ይችላል
ሩሲያ “ሳርማት” የተባለውን አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳዔል በባዛት ማምረት መጀመሯን የሩሲያ ብሄራዊ የስፔስ ኮርፖሬስን (ሮስኮሞስ) አስታወቀ።
የሮስኮሞስ ዳይሬክተር ጄነራል ደሚትሪ ሮጎዚን ከ”ሮሲያ 24” ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ “ሳርማት” አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳዔል የምርት ሂደት መጀመሩን አረጋግጠዋል።
እንዲሁም ሩሲያ ሳርማት አህጉር አቋራጭን ለሁለተኛ ጊዜ ለማስወንጨፍ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ያስታወቁት ዳይሩክተር ጄነራል፤ ሁሉም ነገር በተያዘለት መርሃ ግብር መስረት እየሄደ መሆኑን መግለጻውን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
ሩሲያ “ሳርማት” (አውሬው 2) የሚል መጠሪያ ያለውነወ አህጉር አቋራጭ ሚሳዔልን ባሳለፍነው መጋቢት ወር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መሞከሯ ይታወሳል።
በሙከራው ወቅት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ “ሩሲያን ለመፈታተን የሚፈልጉ ጠላቶቻችን ቆም ብለው ሁለት ጊዜ እንዲያስቡ እናደርጋለን” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
እንዲሁም “ሳርማት” አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል በእጅጉ የተለየ መሳሪያ መሆኑን እና ማንኛውም የሚሳዔል መከላከያ ስርዓቶችን የማለፍ አቅም ያለው መሆኑን ገልፀዋል።
አዲሱ የሩሲያ አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል ሙከራ በደቡብ ምዕራብ ሩሲያ ከምትገኘው ፕሌስክ የተወነጨፈ ሲሆን፤ 6 ሺህ ኪሎ ሜትሮችን ከተጓዘ በኋላ በሌላኛው የሩሲያ አካል በሆነችው ሩቅ ምስራቅ ካማችታካ ማረፉ ይታወሳል።
የሩሲያ አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳዔል የቴክኒክና የታክቲክ ብቃታቸው ከፍተኛ እንዲሁም ዘመናዊ የሚሳዔል መከላከያ ስርዓቶችን መቋቋም የሚችል ነው ተብሏል።
“ሳርማት” አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል 15 የኒኩሌር አረሮችን የሚሸከም ሲሆን፤ እስከ 35 ሺህ ኪ.ሜ ርቀት በመብረር ማጥቃት ይችላል።
የሩሲያው ፐሬዝዳንት ፑቲን ባሳለፍነው ሳምንት፤ ሀገራቸው ያዝነው የፈረንጆቹ 2022 መጨረሻ ላይ ሳርማት የተባለውን አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል ለውጊያ እንደምታሰማራ መግለጻቸው ይታወሳል።