ዩክሬን በምስራቃዊ ባክሙት ድል እየቀናት መሆኑን ገለጸች
በመልሶ ማጥቃት የሩሲያ ወታደሮችን እስከ 500 ሜትር ድረስ ማስለቀቅ መቻሏንም ነው ያስታወቀችው
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ምዕራባዊ ባክሙትን ሙሉ በሙሉ ለመያዝ ውጊያው ቀጥሏል ብሏል
በዩክሬኗ ባክሙት ከተማ ምስራቃዊ ክፍል ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም ኬቭ ድል እየቀናት መሆኑን የዩክሬን ጦር ቃልአቀባይ ሰርሂ ቸርቫቲ ተናግረዋል።
“የተሳካ የመከላከልና መልሶ ማጥቃት ዘመቻ ከፍተናል፤ ባለፉት ቀናትም በአንዳንድ አካባቢዎች የሩሲያ ወታደሮች እስከ 500 ሜትር ድረስ እንዲያፈገፍጉ አስገድደናቸዋል” ነው ያሉት ቃል አቀባዩ።
የሩሲያው ቅጥረኛ ቡድን ዋግነር የመሳሪያ አቅርቦት እጥረት እንዳጋጠመው በአዛዡ ይቪግኒ ፕሪጎዚን የሚነሳው ወቀሳም ፍጹም የተሳሳተ መሆኑንና ሩሲያ በየቀኑ ተጨማሪ ሃይልና መሳሪያ እያቀረበች መሆኑን ቸርቫቲ ለዩክሬን ቴሌቪዥን ገልጸዋል።
ሞስኮ ከስሞኑ በባክሙት ፈጣን ድል ለማስመዝገብ የፓራኮማንዶ ሃይል እያስገባች እንደምትገኝም ተገልጿል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ሩሲያ በዩክሬን መዲና ኬቭ እና በሌሎች በርካታ ከተሞች ጥቃት ማድረሷን ገፍታበታለች ብለዋል።
ይህም በሞስኮ ላይ አለማቀፋዊ ጫናው ሊበረታ እንደሚገባ ያሳያል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
በተያያዘ ሩሲያ የግንብት ወር ከገባ ለ9ኛ ጊዜ በኬቭ ላይ የሚሳኤል ጥቃት ማድረሷ ተነግሯል።
በኦዴሳ በተፈጸመ ጥቃትም የአንድ ሰው ህይወት ማለፉና ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የኬቭ ሹሞች ሩሲያ በአውሮፕላን እና ከመርከብ ላይ የምትተኩሳቸውን ሚሳኤሎች እያከሸፍን ነው ቢሉም ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።
ለወራት በተካሄደው ጦርነት የወደመችውና 70 ሺህ ሰዎች ይኖሩባት የነበረችው ባክሙትም በከባድ ውጊያ እየተናጠች ነው ተብሏል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴርም የከተማዋን ምዕራባዊ ክፍል ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ለማስገባት ውጊያው መቀጠሉን ነው ያስታወቀው።