ሩሲያ በኬርሰን በፈጸመችው ጥቃት በጥቂቱ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን ዩክሬን ገለጸች
በደቡባዊ የከተማዋ ክፍል በደረሰው የአየር ድብደባ የመኖሪያ እና የአስተዳደር ህንጻዎች ፈራርሰዋል
ፕሬዚዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ጥቃቱ ንጹሃንን ኢላማ ያደረገ ነው ቢሉም፤ ሞስኮ በተደጋጋሚ ይህን መሰሉን ወቀሳ ማጣጣሏ ይታወሳል
ሩሲያ በዩክሬን ልዩ ነው ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች ዛሬ 10ኛ ወሯን ይዛለች።
ሞስኮ በዚሁ እለት በኬርሰን ከተማ የአየር ድብደባ መፈጸሟም ከኬቭ ባለስልጣናት ውግዛት ገጥሞታል።
በደቡባዊ የከተማዋ ክፍል የተፈጸመው የአየር ድብደባ እስካሁን በጥቂቱ የሰባት ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል ነው የተባለው።
በጥቃቱ የመኖሪያ እና የአስተዳደር ህንጻዎች መፈራረሳቸውን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችም እየወጡ ነው።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ፥ ጥቃት በተፈጸመበት አካባቢ ምንም አይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ አለመኖሩን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ በቴሌግራም ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፥ “በጥቃቱ የደረሰው አሰቃቂ ጉዳት በማህበራዊ ሚዲያዎች እንደ አዲስ ነገር ቢሰራጭም የዩክሬናውያን የየእለት ሰቆቃ ህይወት ይሄው ነው” ብለዋል።
ሩስያ ግድያውን የፈጸመችው ጸብ ለማጫርና በሰዎች እልቂት ለመደሰት ነው ማለታቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል።
ሞስኮ ስለኬርሰኑ ጥቃት እስካሁን ምንም ምላሽ ባትሰጥም ከዚህ ቀደም መሰል ወቀሳዎችን ማስተባበሏ ይታወሳል።
ባለፈው ወር ከኬርሰን የወጣችው ሩስያ ኒፕሮ ከተባለ ወንዝ ላይ ሆነው ጥቃት በመክፈት ከተማዋን ዳግም በእጇ ለማስገባት ጥረት ማድረጓን ስለመቀጠሏም ኬቭ ትገልጻለች።
የሩስያ ዩክሬን ጦርነት 10ኛ ወሩን ከመያዙ ቀናት ቀደም ብሎ ሁለቱም ተፋላሚ ሀገራት ድንገተኛ ጉብኝቶችን አድርገዋል።
ዜለንስኪ በሚስጢር ወደ አሜሪካ ሲያቀኑ የሩስያ የደህነንት ምክትል ሊቀመንበር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ቤጂንግ ገብተዋል።
የዋሽንግተንም ሆነ የቤጂንግ ጉብኝታቸው ዛሬ 300ኛ ቀኑን የያዘው ጦርነት በእጅ አዙር ጦርነቱን የሚቀላቀሉትን እያበዛ የአለም የደህንነት ስጋት ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ መሆኑን ያሳያል።