አሜሪካ ለዩክሬን የ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ጦር መሳሪያ እንደምትሰጥ ገለጸች
አሜሪካ ባለፉት 10 ወራት ውስጥ ለዩክሬን የ22 ቢሊዮን ዶላር ጦር መሳሪያ ድጋፍ አድርጋለች
የፕሬዝዳንት ዘለንስኪን ጉብኝትን ተከትሎ አሜሪካ ከዚህ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች
አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ የ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ጦር መሳሪያ እንደምትሰጥ ገለጸች።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 10 ወራት የሞላው ሲሆን ጦርነቱ በየጊዜው በአዳዲስ መልኮችን ማሳየቱን ቀጥሏል።
በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት የሚመራው ጥምረት ዩክሬን የሩሲያን ጦር እንድትመክት የጦር መሳሪያ፣ ጥሬ ገንዘብ እና ወታደራዊ መረጃዎችን መስጠታቸውን ቀጥለዋል።
አሜሪካ ብቻዋን ጦርነቱ ከተጀመረበት ካሳለፍነው የካቲት ወር ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ለዩክሬን 22 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያዎችን ለግሳለች።
አሁን ደግሞ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ለዩክሬን ለመስጠት መወሰኗን ሮይተርስ ዘግቧል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ድጋፉን አስመልክተው እንዳሉት "ሩሲያ የቅዝቃዜ ወራትን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ዩክሬናዊያንን በብርድ ለመቅጣት እየሰራች ነው" ብለዋል።
ዩክሬን ከሩሲያ የሚቃጡባትን የአየር ላይ ጥቃቶች እንድትቋቋም አሜሪካ እና አጋሮቿ የጦር መሳሪያ እና ሌሎች ድጋፎችን ይቀጥላሉ ሲሉም ብሊንከን አክለዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ በትናንትናው እለት በሚስጢር ወደ ዋሽንግተን ያቀኑ ሲሆን ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር በመወያየት ላይ ናቸው።
የፕሬዝዳንቱን ጉብኝት ተከትሎም አሜሪካ አዲስ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንደምታደርግ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ሩሲያ በበኩሏ ለዩክሬን የሚደረግ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዲቆም አሳስባ ድጋፉ በዚሁ ከቀጠለ ከአሜሪካ ጋር የቀጥታ ጦርነት ሊጀመር እንደሚችል አስጠንቅቃለች።
አሜሪካ ለዩክሬን እሰጣለሁ ካለቻቸው የጦር መሳሪያዎች መካከል የአጭር ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል ጥቃቶችን መፈጸም እና ማምከን የሚያስችሉ ባልስቲክ ሚሳኤሎችን ያካትታል ተብሏል።
የኔቶ አባል ሀገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ሲሰጡ ቢቆዩም አብዛኞቹ ሀገራት አሁን ላይ ልገሳቸውን ያቆሙ ሲሆን የጦር መሳሪያ ክምችታቸው መመናመኑ ደግሞ ድጋፉን ለማቆማቸው ዋነኛው ምክንያት ነው።