በጎፋ ዞን በደረሰ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ የሟቾች ቀጥር 250 ማለፉ ተነግሯል
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ባሰለፍነው ሰኞ ጠዋት በደረሰ የመሬት መንሸራተትየዜጎች ህይወት ማፉን ተከትሎ የ3 ቀናት ብሔራዊ ሐዘን ታወጀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትበደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ወረዳ የደረሰውን የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከትሎ ሕይወታቸው ላለፉ ዜጎች ለማሰብ ከነገ ጀምሮ ለ3 ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሐዘን አውጇል።
ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫው፤ በደቡብ ኢትዮጵያ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማውን ከፍተኛ ሀዘን በመግለጽ፤ ብሔራዊ የሐዘን ቀን እንዲታወጅ መሰወኑን አስታውቋል።
የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 አንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ /2/ መሠረት ምክር ቤቱ በሥራ ላይ በማይኖርበት ጊዜ የተፈጠረ ክስተት ከሆነ የብሔራዊ የሀዘን ቀንና ሰንደቅ ዓላማው ዝቅ ብሎ የሚውለበለብበትን ሁኔታ በምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ የሚወሰን መሆኑን ይደነግጋል።
በዚህም መሰረት ከሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ ለ3 ቀናት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሽራተት አደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን በማሰብ ብሔራዊ የሀዘን ቀን ሆኖ እንዲታወጅ መወሰኑን ምከር ቤቱ አስታውቋል።
በእነዚህ ቀናት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በሁሉም የሀገሪቱ ግዛቶች፣ በኢትዮጵያ መርከቦች፣ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶች የሪፐብሊኩ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ተወስኗል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ባሰለፍነው ሰኞ ጠዋት በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 257 መድረሱን የተመድ እርዳታ ማስተባበርያ ቢሮ (ኦቻ ) አስታውቋል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል ኦቻ ትናንት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።