ከስታዲየም ውጭ በሚደረገው የፓሪስ ኦሎምፒክ መክፈቻ ምን ይጠበቃል?
አትሌቶች በ100 ጀልባዎች ላይ ኖትረ ዳም እና ሉቭረን ጨምሮ በፓሪስ ዋና ዋና ምልክቶች የሚያደርጉት ጉዞ ተጠባቂ ነው
ከ10 ሺህ በላይ አትሌቶች የሚሳተፉበትን የፓሪስ ኦሎምፒክ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በይፋ ያስጀምሩታል
ተጠባቂው የ2024ቱ ኦሎምፒክ መክፈቻ ዛሬ ምሽት 2 ስአት ከ30 ይጀምራል።
የ128 አመታት እድሜ ያለው ውድድር መክፈቻ ከዚህ ቀደም በትልልቅ ስታዲየሞች ነበር የሚደረገው። የፓሪሱ ግን ለየት ያለ መልክ ያለው ነው።
የዘንድሮው ኦሎምፒክ በስታዲየም ሳይሆን በፓሪስ ታዋቂ ወንዝ “ሴነ” ላይ ነው የሚካሄደው።
አትሌቶች የየሀገራቸውን ሰንደቅ ይዘው በጀልባዎች ላይ በመጓዝ ደማቅ የኦሎምፒክ መክፈቻ ስነስርአት ይካሄዳል ተብሏል።
100 የሚጠጉ ጀልባዎች ተሳታፊ አትሌቶችን ይዘው ኖትረ ዳም እና ሉቭረን ጨምሮ የፓሪስ ዋና ዋና ምልክቶችን ያልፋሉ።
6 ኪሎሜትር የሚረዝመው ደማቅ የጀልባ ጉዞ በኤፍል ታወር ሲጠናቀቅም የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በይፋ የፓሪስ ኦሎምፒክ መከፈቱን ያበስራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የፓሪስና ከመላው አለም ውድድሩን ለመመልከት የተገኙ ተመልካቾችም በሴነ ባህር ዙሪያ ሆነው ተጠባቂውን የኦሎምፒክ መክፈቻ እንደሚከታተሉ ተገልጿል።
ምን ያህል አትሌቶች ይሳተፋሉ?
በፓሪስ ኦሎምፒክ 206 የአለም ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል ሀገራትን የወከሉ 10 ሺህ 500 አትሌቶች ይሳተፋሉ።
በመክፈቻውም በርካታ አትሌቶች ያላቸው ሀገራት በአንድ ጀልባ ጥቂት ተሳታፊ ያላቸው ደግሞ ከሌሎች ሀገራት አትሌቶች ጋር በመጣመር የጀልባ ጉዞውን ያደርጋሉ ተብሏል።
አትሌቶቹ ምን አይነት ልብሶችን ይለብሳሉ?
የፋሽን ከተማዋ ፓሪስ ለኦሎምፒክ ተሳታፊዎች በተለየ ዲዛይን የተሰሩ አልባሳትን አዘጋጅታለች።
የእያንዳንዱ ሀገር አትሌት በተለያዩ የፈረንሳይ ባለሙያዎች በልዩ ዲዛይን የተሰሩ አልባሳትን ለብሰው መክፈቻውን ያደምቁታል።
አልባሳቱ የሀገራትን ባህልና ቅርስ የሚያጎሉ እና የፓሪስ ኦሎምፒክን አይረሴ እንዲሆን በሚያደርግ መልኩ መዘጋጀታቸውን የፈረንሳይ ባለስልጣናት ይፋ አድርገዋል።
በመክፈቻው ማን ያቀነቅናል?
በፓሪሱ ኦሎምፒክ የሙዚቃ ስራቸውን የሚያቀርቡ አርቲስቶች ጉዳይ እስካሁን በሚስጢር ተይዟል።
አስቀድሞ እውቋ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ሲሊንዲዮን በመክፈቻው ትገኛለች ቢባልም ፓሪስ በይፋ አላረጋገጠችም።
ከ400 በላይ ተወዛዋዦች በሴን ወንዝ ዙሪያ በሚውረገረጉበት የኦሎምፒክ መክፈቻ ላይ በአለማቀፍ ደረጃ ዝናን እያተረፉ የሚገኙ ወጣት ሙዚቀኞች ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል።
ምሽት 2 ስአት ከ30 ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው የኦሎምፒክ መክፈቻ አራት ስአታት እንደሚቆይ ተገልጿል።