ጉብኝቱ ሞስኮ ከዩክሬን ጋር ከገባችው ጦርነት በኋላ ለአፍሪካ የሰጠችውን ትኩረት ያሳያልም እየተባለ ነው
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በዚህ ሳምንት የሁለት ቀናት ጉብኝት በማሊ እንደሚያደርጉ የማሊ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል።
ጉብኝቱን የመከላከያና የደህንነት ግንኙነቶችን ለማጠናከር የጋራ ፍላጎት ነጸብራቅ መሆኑን ተገልጿል።
ላቭሮቭ ሰኞ ባማኮ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የምዕራብ አፍሪካዊቷን ሀገር በይፋ ሲጎበኙ የመጀመሪያ ይሆናልም ተብሏል።
ጉብኝቱ ሞስኮ ከዩክሬን ጋር በገባችው ጦርነት ምክንያት ከምዕራባውያን ኃያላን ጋር ፍጥጫ ውስጥ ባለችበት ወቅት በአፍሪካ ያላትን ተደራሽነት ለማራዘም የሰጠችውን ትኩረት ያሳያል ተብሏል።
በፈረንጆቹ 2020 በመፈንቅለ መንግስት ወደ ስልጣን የመጣው የማሊ ወታደራዊ ገዥው ከጎረቤቶች እና ከምዕራባውያን ሀገራት ጋር በምርጫ መዘግየትና እስላማዊ አማጽያንን ለመዋጋት የሩሲያን ቅጥረኛ ወታደሮቸ ለማሰማራት ባደረገው ውሳኔ ፊቱን ወደ ሞስኮ አዙሯል።
"ይህ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ጉብኝት የሽግግር መንግስቱ ስልታዊ አጋርነትን ለማሳደግ ከተወሰደው የፖለቲካ ምርጫ ጋር የተጣጣመ ነው" ሲል የማሊ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በመግለጫው ተናግሯል።
የላቭሮቭ ጉብኝት "የማሊና የሩሲያ መሪዎች ለወዳጅነትና ለሁለትዮሽ ትብብር ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎች በተለይም በመከላከያ እና ደህንነት ላይ ያላቸው ጽኑ ፍላጎት አዲስ ተነሳሽነት ነው" ብሏል።
ማሊ ከአልቃይዳና እስላማዊ መንግስት ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎችን በመዋጋት ላይ ትገኛለች።
ለአስር ዓመታት የዘለቀው ሽምቅ ውጊያ ወደ ጎረቤት ሀገራትም ተዛምቷል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ባለፈው ዓመት የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሞስኮ ታጣቂዎቹን ለማጥፋትና ትብብርን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ለማሊ ተናግረዋል።