የሩሲያ ወታደሮች የአሜሪካ ጦር ወደሚኖርበት የጦር ሰፈር ገቡ
ይህ ተግባር ከፍተኛ ተቀናቃኝ የሆኑት አሜሪካ እና ሩሲያ ወታደሮቻቸው በቅርብ ርቀት እንዲቀመጡ አድርጓል ተብሏል
የሩሲያ ጦር ወደ ኒጀር እንዲገባ የተደረገው በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዘው ጁንታ የአሜሪካ ጦር ለቆ እንዲወጣ መወሰኑን ተከትሎ ነው
በኒጀር፣ የሩሲያ ወታደሮች የአሜሪካ ጦር ወደሚኖርበት የአየረ ኃይል የጦር ሰፈር መግባታቸውን ሮይተርስ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን እንዳረጋገጡለት ዘግቧል።
የሩሲያ ጦር ወደ ኒጀር እንዲገባ የተደረገው በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዘው ጁንታ የአሜሪካ ጦር ለቆ እንዲወጣ መወሰኑን ተከትሎ ነው።
ስልጣን የያዙት ወታደሮች ባለፈው አመት መፈንቅለ መንግስት እስከተደረገበት ድረስ አማጺያንን በመዋጋት ዋነኛ አጋር የነበረችው አሜሪካ 1000 የሚሆኑ ወታደሮቿን እንድታስወጣ ነግረዋታል።
የሩሲያ ጦር ከአሜሪካ ኃይሎች ጋር አለመቀላቀላቸውን እና ከዳይውሪ አለምአቀፍ አየርመንገድ ቀጥሎ ባለው 101 የአየር ኃይል ሰፈር መስፈራቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
ይህ ተግባር በፖለቲካ እና በወታራዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ተቀናቃኝ የሆኑት አሜሪካ እና ሩሲያ ወታደሮቻቸው በቅርብ ርቀት እንዲቀመጡ አድርጓል ተብሏል።
የአሜሪካ ወታደሮች ሲወጡ በሀገሪቱ የተቋቋሙ መሰረተ ልማቶች እጣፈንታ ምን ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄ አስነስቷል።
ባለስልጣኑ "ሁኔታው ጥሩ አይደለም፤ ነገርግን በአጭር ጊዜ የሚስተካከል ነው" ማለታቸውን ዘገባው አክሎ ጠቅሷል።
የአሜሪካ ወታደሮች ከሩሲያ ወታደሮች በቅርብ ርቀት መስፈራቸው ችግር ይፈጥር እንደሆነ የተጠየቁት የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ሊዮድ ኦስቲን የሩሲያ ኃይሎች የአሜሪካ ጦር ወደአለበት መግባት የሚችሉበት እድል የለም በማለት ስጋቱን አጣጥለውታል።
ከኒጀር በጨማሪ በርካታ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ከቀድሞ ቅኝ ገዥዎቻቸው እና ከምዕራባውያን ጋር ያላቸውን ግንኙነት እየቀነሱ፣ በምትኩ ከሩሲያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዋ ግንኙነት እያጠናከሩ ናቸው።
የአሜሪካ ወታደሮች በቅርቡ ከቻድ ተባረዋል። ፈረንሳይም ከማሊ እና ከቡርኪናፋሶ ወታደሮቿን ማስወጣቷ ይታወሳል።