ኒጀር ከአሜሪካ ጋር ያላትን ወታደራዊ ግንኙነት ብታቋርጥም፣ የኢኮኖሚ እና የዲፕሎማሲ ግንኙነቷን ትቀጥላለች ተብሏል
አሜሪካ ወታደሮቿን ከኒጀር ልታስወጣ ነው ተባለ።
አሜሪካ ወታሮቿን ከኒጀር ልታስወጣ መሆኑን እና በዚህ ጉዳይ የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኩርት ካምቤል እና የኒጀር አመራሮች መስማማታቸውን ሮይተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
አሜሪካ በሀገሪቱ 'አየር ቤዝ 2ዐ1' ተብሎ የሚጠራውን የድሮን ማዘዣ ጣቢያ ጨምሮ ሁለት የጦር ካምፖች በ100 ሚሊዮን ዶላር ያቋቋመች ሲሆን ከእነዚህ ካምፖች የሚንቀሳቀሱ ከ1000 በላይ ወታደሮች አላት።
ካምፖቹ ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ እስላማዊ ታጣቂዎችን እና በሳህል ቀጠና የሚንቀሳቀሰውን የአል ቃኢዳ አጋር የሆነውን ጀማኣት ኑስራት አል እስላም ዋል ሙስሊሜን ለማጥቃት ጥቅም ላይ ውለዋል።
የኒጀር ጦር ባለፈው አመት መፈንቅለ መንግስት በማድረግ ስልጣን ተቆጣጥሯል። መፈንቅለ መንግስት እስከተካሄደበት ጊዜ ድረስ ኒጀር የአሜሪካ እና የፈረንሳይ ቁልፍ አጋር ነበረች።
ነገርግን አዲሶቹ የኒጀር ባለስልጣናት እንደ ፈረንሳይ እና አሜሪካ ከመሳሰሉት ምዕራባውያን ጋር ያላቸውን አጋርነት በማቋረጥ እንዲሁም ከቀጣናዊ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጥምረቶች ራሳቸውን በማግለል በጁንታ የሚመሩትን ማሊን እና ቡርኪና ፋሶን ተቀላቅለዋል።
ኒጀር የምዕራባውያን ተቀናቃኝ ከሆነችው ሩሲያ ጋር ግንኙነቷን እያጠናከረች ነው።
ኒጀር ከአሜሪካ ጋር ያላትን ወታደራዊ ግንኙነት ብታቋርጥም፣ የኢኮኖሚ እና የዲፕሎማሲ ግንኙነቷን ትቀጥላለች ተብሏል።
ባለፈው ሳምንት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኒጀራውያን በኒጀር ዋና ከተማ በመውጣት የአሜሪካ ጦር ከሀገራቸው እንዲወጣ ጠይቀው ነበር።