የ53 አመቷ ሩሲያዊ በ31 አመት የሚበልጡትን “ልጃቸውን” ማግባታቸው ቁጣ አስነሳ
አዛውንቷ ከማደጎ ቤት የወሰዱትን ታዳጊ ለስምንት አመት በቤታቸው አሳድገው አግብተውታል ተብሏል
ጋብቻው በማደጎ ልጆች ላይ የሚፈጸም ወሲባዊ ትንኮሳ ማሳያ ተደርጎ እየተነሳ ነው
በሩሲያ የ53 አመቷ አዛውንት ያሳደጉትንና በ30 አመት የሚበልጡትን ወጣት ማግባታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
ከሞስኮ 800 ኪሎሜትር ርቃ በምትገኘው ታታርሳን ታዋቂ ሙዚቀኛ የሆኑት አስይሉ ቺዝቬስካያ ሚንጋሊም ሙዚቃ ሲያስተምሩ ነው የ13 አመቱን ዳኒል የተዋወቁት።
አይሱ በካዛን ከተማ የማደጎ ትምህርት ቤት ሙዚቃ ሲያስተምሩ ያገኙት ዳኒል ድንቅ ተሰጥኦውን በመመልከታቸው ወደ ቤታቸው ወስደውት ሙዚቃን በጋራ መጫወት ይጀምራሉ።
አይሱ እና ዳኒል በተለያዩ የሙዚቃ ዝግጅቶች ላይም በጋራ በመጫወት ተወዳጅነትን እያተረፉ መጥተው ከታዋቂው የሩሲያ ሙዚቀኛ ፊሊፕ ኪርኮሮቭ ጋር እስከመስራት ደርሰዋል።
ላለፉት ስምንት አመት ልክ እንደልጅ እና እናት በጋራ ሲሰሩ የቆዩት አይሱ እና ዳኒል ከቀናት በፊት በጋብቻ መተሳሰራቸውን ይፋ ማድረጋቸው ግን ግርምት መፍጠሩን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።
“የእኛ ጋብቻ ልዩ ደረጃ ያለው ነው፤ በፈጠራ የተሳሰረ ቤተሰብ በምንም መንገድ ግንኙነቱ አይበጠስም” የሚሉት የ53 አመቷ ሙዚቀኛ፥ ሰዎች የሁለቱን ግንኙነት ባለመረዳታቸውን መደናገጣቸውን ይናገራሉ።
“’ዳኒል ለሙዚቃ ነው የተፈጠረው፤ ያለበት እድሜ ደግሞ ጦር መሳሪያ የሚያነግትበት ነው፤ እናም እንዴት ከዚህ ልጠብቀው ብዬ ሰዎችን ስጠይቅ አግቢው አሉኝ” ሲሉም ያክላሉ።
የታታርሳን ነዋሪዎች ግን የእድሜ ልዩነቱ ብቻ ሳይሆን የማደጎ ልጅን ማግባት የሀገርን ክብርንም ዝቅ የሚያደርግ አሳፋሪ ተግባር ነው በማለት ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።
ተቃውሞው ሲበዛም አይሱ የሚያሳድጓቸው ሌሎች አምስት ልጆች ወደ ሌላ የህጻናት ማሳደጊያ ስፍራ ተወስደዋል።
የ53 አመቷ አዛውንት ግን በሙዚቃ እና በመለኮታዊ ሃይል የተጣመረን የሚለየው የለም፤ እድሜ ወይም አካላዊ ነገር ለትዳር መሰረታዊ አይደለም ባይ ናቸው።
ለስምንት አመት ካሳደጉት “ልጃቸው” ጋር ቀለበት አደረጉ የሚለው የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን ርዕሰ ጉዳይ ቢሆንም ከ22 አመቱ ባለቤታቸው ጋር ሙዚቃ በመስራትና በመስማት ሊያሳልፉት ቆርጠው ተነስተዋል።