ሩሲያውያን ሴቶች ባሎቻቸው በዩክሬን እንዲዋጉ ፍላጎታቸው የጨመረው ለምንድን ነው?
ፕሬዝዳንት ፑቲን በሀምሌ ወር የሩሲያን ጦር ለሚቀላቀሉ በጎፈቃደኞች የሚከፈለው ጉርሻ (ቦነስ) በእጥፍ እንዲጨምር ማድረጋቸው ይታወሳል

የአንድ ሩሲያዊ ወታደር ዝቅተኛ አመታዊ የአገልግሎት ክፍያው 3 ነጥብ 25 ሚሊየን ሩብል ነው
ሩሲያውያን ሴቶች ባሎቻቸውና የቀድሞ ፍቅረኞቻቸውን ወደ ዩክሬኑ ጦርነት የመላክ ፍላጎታቸው መጨመሩ ተነገረ።
የብሪታንያው ዴይሊ ኤክስፕረስ ጋዜጣ እንዳስነበበው ሴቶች የትዳር አጋራቸውን ወደ ዩክሬን እንዴት መላክ እንደሚችሉ በኦንላይን የሚያቀርቡት ጥያቄ ከ20 እጥፍ በላይ ጨምሯል።
ሩሲያውያን እንደ ጎግል መረጃዎችን በሚያፈላልጉበት "ያንዴክስ"፥ "ባለቤቴን በዩክሬኑ ልዩ ዘመቻ እንዲዋጋ የምልከው እንዴት ነው?" የሚሉ ጥያቄዎች በብዛት እየቀረበ ነው ይላል ዘገባው።
ሩሲያ በየካቲት ወር 2022 በዩክሬን የጀመረችውን ጦርነት "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ነው የምትለው። በሂደት ጦርነት እያለች ብትገልጸውም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የዩክሬኑን "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ጦርነት ብሎ መጥቀስ እስከ 15 አመት ያስቀጣ እንደነበር ዴይሊ ኤክስፕረስ አስታውሷል።
ሩሲያውያን ሚስቶች ባሎቻቸውን ወደ ዩክሬን የመላክ ፍላጎታቸው የጨመረው ለአባት ሀገራቸው ከመቆርቆር ባሻገር ሌላ ምክንያት ስላላቸው ነው ይላል ዘገባው።
በሀምሌ ወር 2023 በኦንላይን ጥያቄውን የሚያቀርቡት በወር ከ200 አይበልጡም ነበር፤ በነሃሴ 2024 ግን አሃዙ ወደ አምስት ሺህ ከፍ ብሏል።
የኦንላይን ጥያቄዎቹን ያጠኑ ተመራማሪዎች የሩሲያውያን ሴቶች ባሎቻቸውን ወደ ዩክሬን የመላክ ፍላጎት የጨመረው የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለወታደሮች ማበረታቻዎችን ይፋ ባደረጉ ማፍስት ነው።
ፑቲን በሀምሌ ወር የሩሲያን ጦር ለሚቀላቀሉ በጎፈቃደኞች የሚከፈለውን ጉርሻ (ቦነስ) እና ወርሃዊ ደመወዝ በእጥፍ ለመጨመር የሚያስችል ህግ መፈረማቸው ይታወሳል።
አዲስ ምልምሎች በአሁኑ ወቅት እንደተመዘገቡ 400 ሺህ ሩብል (3 ሺህ 921 ዶላር) ይከፈላቸዋል። ወርሃዊ ደመወዛቸውም ወደ 2 ሺህ ዶላር ከፍ ብሏል።
በዩክሬኑ ጦርነት የሚሳተፉ የሩሲያ ወታደሮች ዝቅተኛ አመታዊ ደመወዝ 3 ነጥብ 25 ሚሊየን ሩብል (31 ሺህ 859 ዶላር) ነው የሚለው የዴይሊ ኤክስፕረስ ጋዜጣ፥ በአንጻሩ የሩሲያውን መደበኛ ሰራተኞች አማካይ አመታዊ ደመወዝ 12 ሺህ ዶላር መሆኑን ጠቅሷል።
ወታደሮች ከሩሲያ ጦር ሲለቁ የቤት መግዣ እና ሌሎች መሰረታዊ ወጪዎች ላይ የ50 በመቶ ቅናሽ ይደረግላቸዋል። በየወሩ 2 ሺህ ዶላር ይከፈላቸዋል፤ ወደ ቀደመ ስራቸው የመመለስና ልጆቻቸውን ዩኒቨርሲቲ ለማስገባትም ቅድሚያ ይሰጣቸዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው በ2023 490 ሺህ በጎፈቃደኞች በዩክሬን ለመዋጋት ተመዝግበዋል። በያዝነው የፈረንጆቹ አመትም እስከ ሀምሌ ድረስ 190 ሺህ አዲስ ምልምሎች የሩሲያን ጦር ተቀላቅለዋል።