ዩክሬናውያን ታዳጊዎች ከወታደራዊ ምልመላ ለማምለጥ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እየተጋፈጡ ነው ተባለ
መንግስት እድሜያቸው ከ18 እስከ 60 የሚሆኑ ወንዶች ከሀገር እንዳይወጡ ከልክሏል
በቅርቡ የወጡ ሪፖርቶች በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ጦሩን እየከዱ መሆናቸውን አመላክተዋል
በርካታ ዩክሬናውን ታዳጊዎች በወታደራዊ ምልመላ እና ከሀገር ለመሰደድ በሚደረጉ ሙከራዎች መካከል በአጣብቂኝ ውስጥ እንደሚገኙ ተነገረ፡፡
ዜጎች በአስገዳጁ የብሔራዊ ውትድርና ላለመሳተፍ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እየተጋፈጡ እንደሚገኙ ሮይተርስ አስነብቧል፡፡
ከሩስያ ጋር በምታደርገው ጦርነት በወር እስከ 30 ሺህ የሚጠጉ አዳዲስ ምልምሎች እንደሚያስፈልጓት የሚነገርላት ዩክሬን የብሔራዊ ውትድርናውን ለማምለጥ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ በተያዙ ዜጎች ላይ ቅጣቶችን እየጣለች ነው፡፡
በአሁኑ ወቀት የአዳዲስ ተመልማዮች መመዝገቢያ እድሜ ከ25 አመት የሚጀምር ቢሆንም ሀገሪቱ እያጋጠማት ከሚገኘው የሰው ሀይል እጥረት አንጻር የመመልመያ እድሜ መነሻን ወደ 18 ዝቅ እንድታደርግ በአሜሪካ ተጠይቃለች፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በትላንትናው እለት ከሬውተርስ ጋር ባደረጉት ቆይታ “ዩክሬን የጦርነቱን አካሄድ ለመቀየር ከባባድ ውሳኔዎችን መወሰን አለባት፤ ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት እድሜያቸው ከ18-25 የሚገኙ ወጣቶች በጦርነቱ እየተሳተፉ አይደለም ይህ ጉልበት የጦሩን አቅም ለማጠናከር የሚያግዝ ነው” ብለዋል፡፡
የፕሬዝዳንት ዘለንስኪ አስተዳደር የአጋሮቹን ምዕራባውያን ጫና ተከትሎ ከ18 አመታት ጀምሮ የሚገኙ ወጣት እና ታዳጊዎች ወደ ግንባር እንዲገቡ ምልመላ የሚጀምር ከሆነ ሀገር ጥሎ ለመሰደድ የሚጥሩ ዜጎችን ቁጥር እንደሚጨምረው ተዘግቧል፡፡
በቅርቡ የወጡ መረጃዎች በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የጦር አባላት ለዕረፍት በወጡበት እና ከውግያ ግንባር ላይ ጦሩን እየከዱ እንደሚገኙ አመላክተዋል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረበት 2022 አንስቶ ከ190 ሺህ በላይ የሚሆኑ እድሜያቸው ከ14-17 የሚጠጉ ዩክሬናውያን ታዳጊዎች በጦርነቱ ላለመሳተፍ ጥበቃ እንዲደረግላቸው በአውሮፓ ህብረት ተመዝግበዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዩክሬን ጦር ውስጥ እያገለገሉ የሚገኙ ወታደሮች አማካኝ እድሜ 40 ሲሆን በበዛት በፍቃደኝነት ላይ ጦሩን የሚቀላቀሉት ደግሞ ከ32 አመት በላይ የሆኑ ዜጎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከጦርነቱ በፊት 41 ሚሊየን ዜጎች የነበራት ሀገር 7 ሚሊየን ዜጎቿ ግጭቱን ተከትሎ ወደ ተለያዩ ሀገራት ተሰደዋል፡፡
ባሳለፍነው ማክሰኞ የዩክሬን ፓርላማ “ብሔራዊ አንድነት” የተሰኘ አዲስ ሚኒስቴር መስርያ ቤት አቋቁሟል፡፡
ይህ ተቋም ከሀገር የወጡ ዜጎች ተመልሰው ለሀገራቸው ሉዓላዊነት እንዲፋለሙ የሚያግዙ ፖሊሲዎችን የሚያዘጋጅ እና ጦሩን ተቀላቅለው ሊያገለግሉ የሚችሉ ተጨማሪ ሰዎች ከሀገር እንዳይወጡ የተለያዩ ዘዴዎችን የሚቀይስ ነው ተብሏል፡፡
ፓርላማው ዜጎች በየጦር ግንባሩ ለሀገራቸው ነጻነት እየተዋደቁ በሚገኙበት ወቅት ሌሎች ደግሞ በተመቻቸ ሁኔታ ላይ እየኖሩ መሆናቸው “አሳፋሪ ነው” ሲል ወቅሷል፡፡