ወታደሮቹ የሚጠፉት አዋጊዎች እና አዛዦች በሚሰጡት የተዳከመ አመራር ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል
ከ100 ሺህ በላይ የዩክሬን ወታደሮች ከጦር ግምባር መጥፋታቸው ተገለጸ
አንድ ሺህ ቀን ያለፈው የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት በርካታ አዳዲስ ነገሮችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡
ዩክሬን በየጊዜው የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እያደረገች ሲሆን 100 ሺህ ያህል ወታደሮቿ ከጦር ግምባር ጠፍተዋል ተብሏል፡፡
ዩሮ ኒውስ ከጦር ግምባር የጠፉ ወታደሮችን፣ ወታደራዊ አመራሮችን እና ተንታኞችን አነጋግሮ በሰራው ዘገባ ወታደሮች የመዋጋት ፍላጎታቸው በየጊዜው እየቀነሰ መጥቷል ብሏል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ የዩክሬን ወታደሮች ሳያስፈቅዱ ከጦር ግምባር መጥፋት፣ የመዋጋት ፍላጎት ማነስ፣ ለፈቃድ በሚል ከወጡ በኋላ በዛው መጥፋት እና ሌሎችም ተያያዥ ችግሮች አጋጥሟቸዋል፡፡
የዩክሬን ጦር በዚህ ምክንያት እየተፈተነ ነው የተባለ ሲሆን ክስተቱ ደግሞ ለሩሲያ እንደ ትልቅ አጋጣሚ ተወስዷል፡፡
ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ ከጦር ግምባር ያመለጠ የዩክሬን ወታደር እንዳለው ከሆነ አዋጊዎች እና አመራሮች የሚሰጡት አመራር ደካማ ነው፣ በቅርባችን የሉም በየዕለቱ ጓዶቻችን እንደቀልድ በሩሲያ ጦር ይገደላሉ ሲል ተናግሯል፡፡
ባንድ በኩል እኛ እየተዋጋን በሌላ በኩል ያሉት ግን ለእኛም ሳይነግሩን ለቀው ከአካባቢው ይሰወራሉ፣ የሩሲያ ወታደሮች በቀላሉ ብዙ ቦታዎችን ይቆጣጠራሉ ሲልም ሁኔታውን በምሬት ተናግሯል ተብሏል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወታደር ደግሞ በውጊያ ውስጥ ለቆዩ ወታደሮች የሚደረገው የስነ ልቦና ድጋፍ አነስተኛ መሆኑ በህክምና ሰበብ የሚጠፉ ወታደሮች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል ብሏል፡፡
የሩሲያ ጦር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ በርካታ ቦታዎችን እየተቆጣጠረ ነው የተባለ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ በዩክሬን በኩል ያለው የመከላከል አቅም አነስተኛ በመሆኑ ነው፡፡
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነትን እንደሚያስቆሙ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት የተናገሩ ሲሆን ለዚህ ተልዕኮም የቀድሞ የአሜሪካ ጦር አመራርን ሾመዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በበኩላቸው ከሩሲያ ጋር ያለባቸው ጦርነቱ የሚቋጨው አንድም በሀይል ሁለትም በዲፕሎማሲ ብቻ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡