በዳርፉር ተመቶ በወደቀው አውሮፕላን ሩሲያውያን ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተነገረ
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል በግብጻውያን ሲበር ነበር ያለውን አውሮፕላን መትቶ መጣሉን ገልጿል
በጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ሃይል ግብጽ የሱዳን ጦርን በማገዝ የአየር ጥቃት እየፈጸመች ነው ሲል ይከሳል
በሱዳን ተመቶ በወደቀው አውሮፕላን ሩሲያውያን ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተነገረ።
በካርቱም የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ በዳርፉር በወደቀው ሩሲያ ሰራሽ አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ ሩሲያውያንን እጣ ፈንታ እያጣራ መሆኑን ገልጿል።
“ኢልዩሺን አይኤል -76” የተሰኘው ሩሲያ ሰራሽ የጭነት አውሮፕላን በሱዳን ጦር ወደተያዘችው ኤል ፋሸር መድሃኒትና ሌሎች ቁሳቁሶችን ጭኖ ሲጓዝ ነበር ተብሏል።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አርኤስኤፍ) በግብጽ ጦር አብራሪዎች ሲበር ነበር ያለውን የሩሲያው አውሮፕላን መትቶ እንደጣለው ከትናንት በስቲያ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የሚመራው አርኤስኤፍ ግብጽ የሱዳን ጦርን ለማገዝ የምትፈጽማቸው የአየር ድብደባዎች የንጹሃንን ህይወት እየቀጠፉ ነው ሲል ይከሳል።
ካይሮ ግን 18ኛ ወሩን በያዘው ጦርነት ለሱዳን ጦር ወታደራዊ ድጋፍ እያደረገች ነው በሚል የሚቀርብባትን ወቀሳ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች።
በዳርፉር ተመቶ ስለወደቀው ሩሲያ ሰራሽ አውሮፕላን ዛሬም እየወጡ የሚገኙ መረጃዎች ማብራሪያ የሚሹና አሻሚ ናቸው።
አውሮፕላኑ ሶስት ሱዳናውያን እና ሁለት ሩሲያውያንን አሳፍሮ እንደነበርና ከቻድ ድንበር አካባቢ ተነስቶ ወደ ኤል ፋሸር ሲጓዝ መመታቱን ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል።
የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በበኩሉ የአውሮፕላኑን ጥቁር ሳጥን (ብላክ ቦክስ) እና የጉዞ ሰነዶችን ማግኘቱን የገለጸ ሲሆን፥ ከግብጽ ጋር ስላለው ግንኙነት ግን ማስረጃ አላቀረበም።
የአቪየሽን ባለሙያዎች አውሮፕላኑ የቴክኒክ ችግር ገጥሞት ተከስክሶ ሊሆን ይችላል ቢሉም የሱዳን ጦርም ሆነ አርኤስኤፍ ግን ተመቶ ስለመውደቁ ገልጸዋል።
በካርቱም የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ስለገጠመው አደጋ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ከሱዳን ጦር ጋር በትብብር እየሰራሁ ነው ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል።
የጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ በ2023 ሚያዚያ ወር የጀመሩት ጦርነት ከ10 ሚሊየን በላይ ሱዳናውያንን ከመኖሪያቸው አፈናቅሏል።
በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሪሎ በግንቦት ወር 2024 በጦርነቱ 150 ሺህ የሚጠጉ ሱዳናውያን ህይወታቸው ሳያልፍ እንዳልቀረ መናገራቸው ይታወሳል።