አዲሱ የኬንያ ፕሬዝዳንት ለአፍሪካ ሀገራት የእዳ ስረዛ እንዲደረግ ጠየቁ
ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ “የዕዳ ክፍያ ጫና በአህጉሪቱ የተገኘውን የእድገት ጠራርጎ ሊያጠፋው ይችላል” ብለዋል
የፕሬዝዳንቱ የዕዳ ስረዛ ጥሪ የመጣው በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ያለባቸውን እዳ ለመክፈል ስጋት ላይ በወደቁበት ወቅት ነው
አዲሱ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የበለጸጉ ሀገራት እና አለምአቀፍ አበዳሪዎች በድሃ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ያሉ የዕዳ ጫናዎችን እንዲገመግሙ ጠይቀዋል።
ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው ይህንን ጥሪ ያቀረቡት።
የኬንያው ፕሬዝዳንት በንግግራቸው በደሃ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ያለው ከፍተኛ የእዳ ክፍያ ጫና በአህጉሪቱ የተገኙ የእድገት ውጤቶችን ጠራርጎ ሊያጠፋው ይችላል ብለዋል።
በተለይ የአፍሪካ ሀገራት በግጭት እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ ጫናዎች እንደነበሩባቸውም ተናግረዋል።
የምስራቅ እና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ግጭቶች እና ለውጦች በቀጣናው ልማት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ፈተና መደቀናቸውንም ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ለተመድ ጉባዔ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
በእነዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች የበለጸጉ ሀገራት እና አለምአቀፍ አበዳሪዎች በደሃ የአፍሪካ ሀገራት የዕዳ ጫናን ለማቅለል የእዳ ስረዛ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
የፕሬዝዳንቱ የዕዳ ስረዛ ጥሪ የመጣው በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ያለባቸውን እዳ ለመክፈል ስጋት ላይ በወደቁበት ወቅት መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
የኬንያ ብሄራዊ ባክ መረጃ እንደሚያመለክተው ኬንያ ባሳለፍነው ዓመት ያለባትን ብድር ለመክፈል 6 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ወጪ ያደረገች ሲሆን፤ ይህም መንግስት ከታከስ እና ከሌሎች ዘርፎች ከሰበሰበው ገቢ ከግማሽ በላይ እንደሆነም ተነግሯል።
በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የበለጸጉ ሀገራት እንዲሁም እንደ አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) እና የዓለም ባንክ የሚከፍሉት የእዳ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎ ይጠቁማሉ።
በብዛት እየተከፈሉ ያሉ እነዚህ እዳዎች በአፍሪካ ሀገራት ያሉ የልማት እቅስቃሴዎችን ሊያቆሙ እንደሚችሉም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።