ሩቶ የመንግስት የስልጣን ዘመን በሁለት አመት እንዲጨምር የወጣውን ረቂቅ ተቃወሙ
የኬንያ ሴኔት የፕሬዝዳንቱን ጨምሮ የፓርላማ አባላት የአገልግሎት ዘመን ከአምስት ወደ ሰባት አመት ከፍ እንዲል ጠይቋል
ፕሬዝዳንቱ የማሻሻያ ረቂቁ ከጥቂት ስልጣን ፈላጊዎች የመነጨ ሀሳብ ነው ሲሉ ተችተውታል
የኬንያ ሴኔት አባላት የመንግስት የስልጣን ዘመንን ለማራዘም ያዘጋጁት ረቂቅ ህግ ከፕሬዛዳንት ዊሊያም ሩቶ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
ፕሬዝዳንቱ የጥቂት ግለሰቦችን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት እና የስልጣን ጊዜ ለማራዘም በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥ አልሳተፍም ብለዋል፡፡
የሀገሪቱ ሴኔት እንዳዘጋጀው በተነገረው የማሻሻያ ረቂቅ በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ የሚገኘው አንድ የስልጣን ዘመን አምስት አመት እንዲሆን የሚወስነውን ህግ ወደ ሰባት ከፍ እንዲል የሚጠይቅ ነው፡፡
በረቂቁ ከፕሬዝዳንቱ በተጨማሪ የምክር ቤት አባላት እና የመንግስት ተሿሚዎች የአገልግሎት ጊዜ በሁለት አመት ከፍ እንዲል ቀርቧል፡፡
የሀገሪቱ ህገ መንግስት አንቀጽ 15 ላይ አንቀጽ "15 ኤ" ተብሎ በሚካተተው ማሻሻያ ኬንያ ከፓርላማው በፕሬዝዳንቱ የሚሾም ጠቅላይ ሚንስትር እንዲኖራትም በተጨማሪነት ይጠይቃል፡፡
የሚሾመው ጠቅላይ ሚንስትር በፓርላማው በርካታ መቀመጫ ካላቸው ፓርቲዎች አልያም ጥምር ፓርቲዎች ውስጥ የሚመረጥ ይሆናል፡፡
የማሻሻያ ረቂቁ ከጥቂት ሰዎች ስልጣን ፍላጎት የመነጨ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ሩቶ ፓርቲያቸው ዩናይትድ ዴሞክራቲክ አላያንስ እና የፓርላማው አባላት ሀሳቡን እንዳይደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪም ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን የሚንዱ ፣ የተረጋጋ ፖለቲካዊ ስርአትን የሚያውኩ እና ህገ መንግስትን የሚንዱ ተግባራትን አጥብቄ እቃወማለሁ ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
የፓርቲው ዋና ጸሀፊ ሃሰን ኦማር የኬንያን የዴሞክራሲ ጉዞ የሚቀለብስ ፣ ለተጠያቂነት እና ግልጽነት የማይመች ለአጠቃላይ ፖለቲካዊ ሂደት ስጋት የሆነ ረቂቅ ነው ሲሉ ተችተውታል፡፡
ምንም እንኳን በስልጣን ላይ ካለው መንግስት እና ፓርቲ ተቃውሞ ቢገጥመውም የሴኔቱ የፍትህ እና የህግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥቅምት 25 ለውሳኔ ከመቅረቡ በፊት ህዝብ አስተያየት እንዲሰጥበት ክፍት አድርጎታል፡፡
በኑሮ ውድነት እና በኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች በከፍተኛ ተቃውሞ ስትናጥ የሰነበተችው ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር አሁን ከምትገኝበት የማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ አንጻር ዜጎች ይህን ረቂቅ በሰፊው ሊቃወሙ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው፡፡