ሩዋንዳ ከ4 ሺህ በላይ ቤተክርስቲያናትና መስጂዶች ዘጋች
የድምጽ ብክለት ማስከተልና የደህንነት ደንቦችን መጣስ ለመዘጋታቸው ምክንያት ሆኖ ቀርቧል
ኪጋሊ ከአምስት አመት በፊት የአምልኮ ስፍራዎችን መስፋፋት የሚቆጣጠር ህግ ማውጣቷ ይታወሳል
ሩዋንዳ የጤናና ደህንነት ደንቦችን የተላለፉ ከ4 ሺህ በላይ ቤተክርስቲያናትና መስጂዶች መዝጋቷን አስታወቀች።
የተዘጉት የአምልኮ ስፍራዎች የድምጽ ብክለትን የሚያስቀሩ መሳሪያዎችን ያልገጠሙ መሆናቸውም ነው የገለጸችው።
ባለፈው ወር የተዘጉት አብዛኞቹ ቤተክርስቲያናት የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች መገልገያዎች ሲሆኑ፥ በወንዞች ዳርቻና በዋሻዎች ዙሪያ የተሰሩ መስጂዶችም ተዘግተዋል ተብሏል።
“ውሳኔው ሰዎች በቤተ እምነቶች ዙሪያ ጸሎት እንዳያደርጉ ለማገድ ሳይሆን የምዕመኑን ደህንነት ለመጠበቅ በማሰብ የተላለፈ ነው” ብለዋል ጄን ክላውድ ሙሳብዪማና የተባሉ ባለስልጣን።
ከተዘጉት 4 ሺህ 223 የአምልኮ ስፍራዎች 427ቱ በዋሻ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን በመጥቀስም አንዳንዶቹ ቤተክርስቲያናት በድንኳን ውስጥ የሚሰጡት አገልግሎት ምዕመናንን ለአደጋ ማጋለጡን ያብራራሉ።
ኪጋሊ ከአምስት አመት በፊት የአምልኮ ስፍራዎችን መስፋፋት የሚቆጣጠር ህግ ማውጣቷ ይታወሳል።
ህጉ የአምልኮ ስፍራዎች ህዝብን የሚያውክ ድምጽ ከማውጣት እንዲቆጠቡና ድምጽ ወደውጪ እንዳይወጣ የሚያፍኑ መሳሪያዎችን እንዲገጥሙ ያዛል።
አዳዲስ ቤተክርስቲያናትን የሚከፍቱ ሁሉም ሰባኪዎች ተገቢውን ሃይማኖታዊ ትምህርትና ስልጠና መከታተላቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ ማቅረብ እንዳለባቸውም ያስገድዳል።
ህጉ በ2018 ተፈጻሚ በሆነበት ወቅት 700 ቤተክርስቲያናት መዘጋታቸውንና በወቅቱ ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ “ሀገራችን በርካታ የአምልኮ ስፍራዎች አያስፈልጋትም” ማለታቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
ካጋሜ የአምልኮ ስፍራዎቹን አገልግሎት ለማስቀጠል የበለጸገ ኢኮኖሚ መገንባት ያስፈልጋል በሚል ደህንነታቸው ያልተጠበቁና ደንበችን የተላለፉ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተክርስቲያናት እንዲዘጉ አድርገዋል።
ተቺዎቻቸው ግን ለአራተኛ የስልጣን ዘመን በቅርቡ የተመረጡት ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ የመናገር እና የእምነት ነጻነትን እየነፈጉ ነው ይሏቸዋል።