አዲሱ የብሪታኒያ ጠ/ሚኒስትር ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ፖሊሲ 'ሞቶ የተቀበረ' ጉዳይ ነው አሉ
ጠ/ሚኒስትር ስታርመር “ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ እቅድ በይፋ ተሰርዟል ብለዋል
ብሪታኒያ ጥገኝነት ጠያቂዎች ጥያቄያቸው ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ በሩዋንዳ እንዲቆዩ የሚያደርግ ህግ አጽድቃ ነበር
አዲሱ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ኬር ስታርመር ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ፖሊሲ 'ሞቶ ተቀበረ' ጉዳይ ነው ሲሉ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚንስትር ኬር ስታርመር ስራ ከጀመሩ በኋላ በሰጡት የመጀመሪያ መግለጫቸው በቀድሞው የወግ አጥባቂ መንግስት ቀርቦ የነበረው አወዛጋቢው የሩዋንዳ የስደት ፖሊሲ መሰረዙን አስታውቀዋል።
ስታርመር ውጤታማ ያልሆኑ እና ኢሰብአዊ የሆኑ የኢሚግሬሽን እርምጃዎችን ለማስቆም ቁርጠኛ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል ነው የተባለው።
ጠቅላይ ሚንስትር ኬር ስታርመር በዳውኒንግ ስትሪት ጽህፈት ቤታቸው ባደረጉት ንግግር የሩዋንዳው የስደተኞች እቅድ ገና ከጅምሮ ሞቶ የተቀበረ ነው ብለዋል።
በፈረንጆቹ 2024 የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ የእንግሊዝን ቻናል የሚያቋርጡ ስደተኞችን ቁጥር በእጀጉ መጨመሩን ያመላከቱት ጠ/ሚኒስትር ስታርመር፤ ይህም ለፖሊሲው ውድቀት ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።
የብሪታኒያ መንግስት ከሁለት ዓመት በፊት በሀገሪቱ የሚገኙ ስተደኞችን በአንድ ነጠላ ትኬት ወደ ሩዋንዳ እንደሚልክ ማሰወቁ ይታወሳል።
ሩዋንዳም በብሪታኒያ የሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እና ስደተኞችን ለመቀበል የሚልየን ዶላሮች ስምምነት ፈርማ ነበር።
ብሪታኒያ፤ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተለይም ከአፍሪካ የሚመጡ ስደተኞች በጥገኝነና በስደተነኝነት የሚኖርባት ሀገር መሆኗ ይታወቃል።
ይህ አከራካሪ ሆኖ እየቀጠለ ያለ ጉዳይ ‘የፈጣሪን ስራ የሚጻረር’ ተግባር መሆኑ ከሃይማኖት መሪዎች ጀምሮ እስከ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሲተቹት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡
የመብት ተሟጋቾች የብሪታኒያ መንግስት ስደተኞችን የመንከባከብ ግዴታውን ለመሸሽ ያደረገው ነው በሚል መንቀፋቸውም አይዘነጋም፡፡