የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠርጣሪ በደቡብ አፍሪካ ተያዙ
የቀድሞው የፖሊስ አባል በ1994ቱ የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል ከፍተኛ ደረጃ ተጠርጣሪዎች መካከል ናቸው
ግለሰቡ በቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ሁለት ሽህ ቱትሲዎች እንዲገደሉ ትእዛዝ ሰጥተዋል በሚል ተጠርጥረዋል
በፈረንጆቹ 1994 በተካሄደው የዘር ማጥፋት ወንጀል ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው የነበሩ ሁለት ሽህ የሚጠጉ ቱትሲዎች እንዲገደሉ ትእዛዝ ሰጥተዋል በሚል የተከሰሱት ሩዋንዳዊ በደቡብ አፍሪካ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የተባበሩት መንግስታት የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አስታውቋል።
የቀድሞ የፖሊስ መኮንን ፉልጀንስ ካይሼማ የሩዋንዳ ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በኪቡዬ ግዛት የኒያንግ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ ከመሰረተባቸው ከ2001 ጀምሮ በስደት ላይ ነበሩ ተብሏል።
ተጠርጣሪው በደቡብ አፍሪካ በወይን እርሻ ላይ በሀሰተኛ ስም ሲሰሩ ተይዘዋል።
ዓቃቢ ህግ “እስሩ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ለዋሉበት ወንጀል በመጨረሻ ፍትህ እንደሚጠብቃቸው ያረጋግጣል” ብሏል።
ካይሼማ በእስር ላይ እንደሚቆዩ እና ለሩዋንዳ ተላልፈው እስኪሰጡ ድረስ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ሮይተርስ ዘግቧል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች እስሩ እንደ ካይሼማ መሰል ወንጀሎችን ለሚፈጽሙ ከባድ መልዕክት ያስተላለፈው ነው ብለዋል።
"ከቅጣት ማምለጥን ማቆም ለሰላም፣ ለደህንነት እና ለፍትህ ወሳኝ ነው" ብለዋል።
በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ወቅት በግምት 800 ሽህ የሚገመቱ የቱትሲ እና የሁቱ ጎሳዎች ተገድለዋል።