ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመ ነው-መንግስት
ኢሰመኮ ከተመድ ጋር በመሆን በሁለቱ ክሎሎች የመብት ጥሰት ምርመራ ሊካሂድ እንደሚችል ገልጿል
መንግስት ጉዳዩ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ተደርጎ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘበው ይደረጋል ብሏል
ህወሃት በአፋር እና በአማራ ክልሎች ዘር ማጥፋት እየፈጸመ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች የጅምላ ግድያዎች መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሰረት ህወሃት በአፋር እና አማራ ክልሎች የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመ ነው ብለዋል፡፡
- የህወሃት ታጣቂዎች በቆቦ “ቤት እያንኳኩ” ሰው እየገደሉ መሆናቸውን የወረዳው አስተዳዳሪና ነዋሪዎች ተናገሩ
- በማይካድራ በአሰቃቂ መንገድ ተገድለው የተገኙ ሰዎች ቁጥር 700 እንደሚደርስ ተገለጸ
- በትግራይ እንደተደረገው ሁሉ በአማራ እና በአፋርም ተመሳሳይ አይነት የጣምራ ምርመራና ሪፖርት ይደረግ ይሆን ?
ከአሁን ቀደም በማይካድራ፣ በጭና፣ በጋሊኮማ፣ በአጋምሳ፤ቆቦ፣ ውርጉሳ፣ ውጫሌ ከምቦልቻና እና በሌሎችም አካባቢዎች ተመሳሳይ ወንጀሎችን የፈጸመው ቡድኑ በንጹሃን ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ ወንጀሉ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጭምር እንዲያውቀው ይደረጋል፤ የመንግስትም ስራው ይሄው ነው ብለዋል፡፡
ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም ይህንኑ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል እንደተደረገው ሁሉ በአማራና አፋር ክልሎች ተመድን ያሳተፈ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ ሊካሄድ እንደሚችል የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በቅርቡ ለአል ዐይን አማርኛ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በፌደራል መንግስትና በህወሃት ሃይሎች መካከል ያለው አለመግባባት ወደ ወታደራዊ ግጭት ከገባ ከ8 ወራት በኋላ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፤ጦሩን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱ ይታወሳል፡፡
ነገርግን በኢትዮጵያ መንግስት በሽብር የተፈረጀው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች ጥቃት መክፈቱንና ይህንም ለመቀልበስ እንደሚንቀሳቀስ መንግስት መግለጹ ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ውስጥ በመንግስት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ጦርነት እየተካሄ የሚገኝ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ከግንባር ሆነው ባስተላለፉት መልእክት፤ ጦርነቱን መንግስት ማሸነፉ የማይቀር ስለሆነ የህወሓት ታጣቂዎች እጃቸውን ለጸጥታ አካላት እንዲሰጡ ጥሩ በትናንትናው እለት ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡