14 ሚሊየን ህዝብ ባላት ሀገር 9.5 ሚሊየን መራጮቸ ለመምረጥ ተመዝግበዋል
ሩዋንዳ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን በማካሄድ ላይ ትገኛለች።
አስከፊ የዘር ጭፍጨፋ ታሪክ ያላት ሩዋንዳ ሰለማዊ ምርጫን በማካሄድ ላይ ትገኛለች፡፡
በሀገሪቱ የነበረውን ደም አፋሳሽ ግጭት ያስቆሙት እና ለ30 አመታት በስልጣን ላይ የዘለቁት ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሚ ለተጨማሪ የስልጣን ዘመን እየተወዳደሩ ነው፡፡
በሀገሪቱ ከዚህ ቀደም የተደረጉትን ሶስት ምርጫዎች ከ93 በመቶ በላይ ድጋፍ ማሸነፍ የቻሉት የ66 አመቱ ካጋሜ ከሁለት እጩዎች ጋር ለፉክክር ቀርበዋል፡፡
14 ሚሊየን ህዝብ ባላት ሀገር የተመዘገቡት 9.5 ሚሊየን መራጮች ከፕሬዝደንት ባለፈ የፓርላማ አባላትን የሚመርጡ ይሆናል፡፡
በምርጫው ለመሳተፍ የካጋሜ አስተዳደር ቀንደኛ ተቃዋሚ ናቸው የተባሉ ስምንት እጩዎች ተመዝግበው የነበረ ቢሆንም የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ከወንጀል ክስ ጋር በተየያዘ እና በሌሎች መስፍረቶች ከውድድሩ ውጭ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
በዘንድሮው ምርጫ የዴሞክራቲክ ግሪን ፓርቲ መሪው ፍራንክ ሀቢኒዛ እና በግሉ የሚወዳደረው ፍሊፕ ፓይማና ለእጩነት ቀርበዋል፡፡
ከህዝቡ በቀረበ ጥያቄ በዘንድሮው ምርጫ መወዳደራቸውን የሚገልጹት ፕሬዝዳንት ካጋሜ “እረፍት ማድረግ እፈልግ ነበር፤ ነገር ግን በምርጫው እንድሳተፍ የሚጠይቁ ዜጎች ቁጥር በመጨመሩ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ወስኛለሁ” ነው ያሉት፡፡
ካጋሚ የስልጣን ዘመንን በማራዘም ለበርካታ ጊዜያት በስልጣን ላይ ከቆዩ የአፍሪካ መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንቱ በፈረንጆቹ 2015 አንድ ፕሬዝዳነት ከሁለት የስልጣን ዘመን ጊዜ በላይ በሀላፊነት እንዳይቆይ የሚደነግገውን ህግ ህዝበ ውሳኔ በማድረግ ሽረዋል፡፡
የዘር ጭፍጨፋውን ከማስቆም ባለፈ የሀገሪቱ ምጣኔሀብት እድገት እንዲያስመዘግብ አስተዳደራቸው አበረታች ስራዎችን እንዳከናወነ የሚናገሩ ዜጎች እንዳሉ ሁሉ፤ ምዕራባውን እና እንዳንድ ተቺዎቻቸው ደግሞ ተቃዋሚዎችን በማሰር፣ ሚዲያዎችን በማፈን እና በኮንጎ የሚዋጉ የኤም 23 አማጺዎችን በመደገፍ ይወቅሷቸዋል፡፡
ለሁለት ተክፍሎ በአመጻ ውስጥ የ100ሺዎችን ህይወት የቀጠፈ ጭፍጨፋ በማስቆም ሀገሪቱን ወደ አንድነት በማምጣት ጥልቅ ሚና አላቸው ብለው የሚያምኑ ዜጎች ፕሬዝዳንቱ በስልጣን ይዘልቁ ዘንድ ፍላጎት አላቸው፡፡
ይህን ተከትሎም ካጋሜ በዚህኛው ምርጫም በከፍተኛ የድምጽ ልዩነት ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ከወዲሁ ቅድመ ግምቱን አግኝተዋል፡፡