ከሰሞኑ የሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ ድንበርን በውጥረት የሞላው ምንድን ነው?
ደቡብ ኮሪያ ከሶስት አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወታደሯ ወደ ሰሜን ኮሪያ ድንበር ተኩሷል
ለተኩሱ የሰሜን ኮሪያ ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ሴኡልን በተጠንቀቅ እንድትጠብቅ አስገድዷል
የደቡብ ኮሪያ ወታደር ባለፈው ቅዳሜ በልምምድ ላይ እያለ ወደ ሰሜን ኮሪያ ድንበር መተኮሱ ሀገራቱን በተጠንቀቅ ላይ እንዲሆኑ አድርጓል።
የደቡብ ኮሪያው ወታደር አራት ጊዜ ጥይቶችን መተኮሱ ነው የድንበር ላይ ውጥረቱን የጨመረው።
በጋንግዋን ግዛት በተደረገ ወታደራዊ ልምምድ ላይ ምንም አይነት ተኩስ ባይኖርም ሰልጣኙ ወታደር በስህተት ወደ ሰሜን ኮሪያ ድንበር አቅጣጫ መተኮሱን የደቡብ ኮሪያው ዮናፕ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ጉዳዩን ወዲያውኑ ለሰሜን ኮሪያ የድንበር ጠባቂዎች የማስረዳት ስራም ተከናውኗል ነው የሚለው ዘገባው።
ሴኡል “ተኩሱ የተከፈተው ሆን ተብሎ አይደለም፤ ጥይቶቹ ያረፉትም በደቡብ ኮሪያ ድንበር ላይ ነው” ብትልም ከፒዮንግያንግ እስካሁን ምንም ምላሽ አልተደመጠም።
የኪም ጆንግ ኡን ሀገር ድምጿን አጥፍታ ልትወስደው ለምትችልውም ምላሽም ታዲያ ደቡብ ኮሪያ ወታደሮቿን በተጠንቀቅ እንዲጠባበቁ አዛለች።ሁለቱ ኮሪያዎች ይህን መሰል ክስተት ካስተናገዱ ሶስት አመታት ተቆጥረዋል።
በፈረንጆቹ መጋቢት 4፣ 2020 የደቡብ ኮሪያ ወታደር ከሰሜን በተተኮሱ አራት ጥይቶች ቆስሎ ሴኡልም ተመሳሳይ ምላሽ መስጠቷ የሚታወስ ነው።
ይህም ሀገራቱ በ2018 ከተፈራረሙት የድንበር ላይ ውጥረትን የሚያረግብ ስምምነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመ እንደነበር የሚያወሳው ዮንሃፕ፥ የሰሞኑ ፍጥጫም ምንም ጉዳት ባያደርስም ሁለተኛው ሆኖ ተመዝግቧል ይላል።
ሀገራቱ በሚሳኤልና ኒዩክሌር ሙከራ የገቡበት ውጥረት ግን ለአመታት ቀጥሏል።የሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ ድንበር በአለማችን ካሉ ጥብቅ ቁጥጥር ከሚደረግባቸው ድንበሮች መካከል ይጠቀሳል።
250 ኪሎሜትር ርዝመት እና 4 ኪሎሜትር ስፋት ያለው ከጦርነት ነጻ የሆነ የጋራ ቀጠናቸውም በአለማችን ውጥረት ካልረገበባቸው አካባቢዎች አንዱ መሆኑ ይታወቃል።
ፒዮንግያንግ ለሰሞኑ “የሴኡል የስህተት ተኩስ” አጻፋውን ልትመልስ ትችላለች የሚለው ግምትም የድንበር ላይ ፍጥጫውን እንሮታል።