ደቡብ ኮሪያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለማግኘት የተለያዩ አማራጮችን እያጣራሁ ነው ብላለች
የአሜሪካ የመከላከያ መስሪያ ቤት ሴኡል በረጅሙ የጥበቃ ጃንጥላ ስር በመሆኗ ደቡብ ኮሪያን ከሰሜን ኮሪያ ለመከላከል ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል ሀገራቸው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ልታሰማራ እንደምትችል ተናግረዋል።
የፔንታጎን የፕሬስ ጸሀፊ ብርጋዲየር ጄኔራል ፓት ራይደር በጋዜጣዊ መግለጫቸው የአሜሪካ ፖሊሲ የኮሪያ ልሳነ ምድርን ሙሉ በሙሉ ከኒውክሌር ነጻ ማድረግ ላይ ትኩረት ማድረጉን ይቀጥላል ብለዋል።
"ብዙዎቹ ከክልላዊ ደህንነት እና መረጋጋት አንጻር እና የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን የመጠቀም እድልን ከመከላከል አንጻር የተያያዘ ነው። የእኛ ፖሊሲ ከኒውክሌር መታጠቅ ጋር በተያያዘ ግን በጣም ግልጽ ነው” ሲሉ ራይደር ተናግሯል።
ነገር ግን የኮሪያ ሪፐብሊክ በተራዘመው የመከላከያ ጃንጥላ ውስጥ መውደቋን ማስታወሱም አስፈላጊ ነው ሲሉም አክለዋል።
የፔንታጎን ቃል አቀባይ እንዳሉት ወደ 30 ሽህ የሚጠጉ ወታደሮቻቸው በደቡብ ኮሪያ ብቻ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ወታደሮቹ አጋሮቻቸውን በመደገፍ እና በመከላከል ላይ ያተኮሩ ናቸውም ብለዋል።
"ለዚህ ዓላማ ያለን ቁርጠኝነት እንደ ብረት የጠነከረ ነው" ሲሉም አክለዋል።
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት የአሜሪካ ታክቲካል የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ወደ ሀገሪቱ ለማስገባት ወይም የራሷን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንድታገኝ የተለያዩ አማራጮችን እያጣራሁ ነው ብለዋል።
በፈረንጆቹ 1990 አሜሪካ ከሶቭየት ህብረት ጋር ትጥቅ የማስፈታት ስምምነትን ተከትሎ ከደቡብ ኮሪያ ታክቲካል የኒውክሌር ጦርን ማስወጣቷን አናዶሉ ዘግቧል።