ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ለ11 ዓመታት የዘጉትን ድንበር ሊከፍቱ ነው
የድንበር መከፈት ዜና የተሰማው ከሰሞኑ በጁባ ጉብኝት ያደረጉት ጠ/ሚ ሃምዶክ ከፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ጋር መወያየታቸውን ተከትሎ ነው
ድንበሩ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ይከፈታል ተብሏል
ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ለ11 ዓመታት የዘጉትን ድንበር እና የድንበር ላይ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመክፈት ተስማሙ፡፡
የድንበር በሩን ለመክፈት ስምምነት ላይ የተደረሰው ከሰሞኑ በጁባ ጉብኝት ያደረጉት የሱዳኑ ጠ/ሚ አብደላ ሃምዶክ ከፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ጋር መወያየታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የድንበር በሩ በመጪው ጥቅምት መባቻ በይፋዊ ስነ ስርዓት እንደሚከፈትም ነው የተነገረው፡፡
የሃምዶክን ጉብንት ተከትሎ ሃገራቱ ትናንት ባወጡት የጋራ መግለጫ በተለያዩ ዘርፎች ለመተባበር የሚያስችል አመርቂ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከአሁን ቀደም ያደረጓቸውን የትብብር ስምምነቶች አፈጻጸም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው በኩል ለመከታተልም ተስማምተዋል፡፡
የጀበለን ሬንክ፣ የሜይራም፣ የቡራህ-ቱምሻህ እና ካርሳና-ፓናኩዋክ የድንበር መተላለፊያዎችን ለመክፈትም ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
ድንበሩ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ይከፈታል ተብሏል፡፡
ጁባ እና ካርቱም የድንበር ላይ ንግድ እና ትራንስፖርትን ፣ የሰውና የጭነት የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎችን ለመክፈት፣ የባንክ እንቅስቃሴን ለመፍቀድና ለማቀላጠፍ አንዱ በአንዱ ሃገር ቅርንጫፍ ባንኮችን የሚከፍትበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፣ በነዳጅና ጋዝ ዘርፍ የጋራ ስልትን ለመቀየስም ተስማምተዋል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስራቤቶቻቸው መካከል ያለውን የቴክኒክ ትብብር እንደገና ለማስጀመር እና በሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲፕሎማሲ ጥናት ማዕከል ውስጥ የደቡብ ሱዳን ዲፕሎማቶችን ለማሰልጠንም ነው ሃገራቱ የተስማሙት።