ግራንዲ በከሰላ እና ገዳሪፍ አካባቢዎች የሚገኙ ስደተኞችን ለመጎብኘት በማሰብ ነው ለ2 ቀናት ጉብኝት ሱዳን የገቡት
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ ሱዳን ናቸው፡፡
ትናንት ምሽት ካርቱም የደረሱት ግራንዲ በከሰላ እና ገዳሪፍ አካባቢዎች የሚገኙ ስደተኞችን ለመጎብኘት በማሰብ ነው ለ2 ቀናት ጉብኝት ሱዳን የገቡት፡፡
ከተለያዩ የኮሚሽኑ የምስራቅ አፍሪካ እና የሱዳን አስተባባሪዎች እንዲሁም የሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ሆነው ከሰላ ወደተሰኘው የሃገሪቱ ክልል አቅንተዋል፡፡
በከሰላ ስደተኞችን እንደሚጎበኙ እና በድጋፍ ሁኔታዎች ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡
ለግራንዲ አቀባበል ያደረጉት አዲሱ የክልሉ አስተዳዳሪ (ዋሊ) ጠይብ መሃመድ አል ሼክ ስለ ኢትዮጵያ ስደተኞች ጉዳይ አንስተው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡
በትግራይ ግጭት ምክንያት በርካቶች ተፈናቅለው በኡም ራኩባ እና በሌሎችም ስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡
በደቡብ ሱዳን የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ ሱዳን ያቀኑት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽነሩ በሱዳን በሚኖራቸው ቆይታ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን ጨምሮ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርያም አል ሳዲቅ እና ሌሎችም የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ ይተበቃል፡፡
በጁባ በነበራቸው ቆይታ ስለ ስደተኞች ጉዳይ ከፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ጋር መክረዋል፡፡
በደቡብ ሱዳን እና ሱዳን የሚገኙ 7 ሚሊዬን ስደተኞችን ጉዳይ ዘላቂ እልባት ለመስጠት ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ጋር በመተባበር በተጀመሩ ስራዎች ዙሪያ ከፕሬዝዳንት ኪር ጋር መምከራቸውንም ነው ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ያስታወቁት፡፡
ፍሊፖ ግራንዲ ከአሁን ቀደም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስደተኞች በሚገኙባቸው የተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡