ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ማስፋፊያ አደርጋለሁ አለ
ኩባንያው በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ 5 ሺህ የኔትወርክ ማማ እንደሚተክል አስታውቋል
ሳፋሪኮም በ2 ሺህ 500 የኔትወርክ ማማዎች አገልግሎት እየሰጠሁ ነው ብሏል
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ማስፋፊያ አደርጋለሁ አለ፡፡
ኢትዮጵያ ለውጭ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ በሯን መክፈቷን ተከትሎ ነበር ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ወደ አዲስ አበባ የመጣው፡፡
ድርጅቱ ዓለም አቀፍ አጋርነት ለኢትዮጵያ በሚል ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ላይ በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ህጋዊ ፍቃድ ከተቀበለ ከአንድ ዓመት በኋላ ስራ ጀምሯል፡፡
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለአል ዐይን እንዳስታወቀው በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ ለኔትወርክ ማስፋፊያ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር መድቤያለሁ ብሏል፡፡
ተቋሙ አክሎም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎችበተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ 5 ሺህ አዳዲስ የኔትወርክ ማማዎችን እንደሚተክልም አስታውቋል፡፡
ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በተደረገ የሁለትዮሽ ስምምነት የኔትወርክ አገልግሎቱን ለደንበኞቹ እየሰጠ መሆኑን ያሳወቀው ሳፋሪ ኮም ቀስ በቀስ የራሱን የኔትወርክ መስመሮች እየገነባ እንደሆነም ገልጿል፡፡
አሁን ላይ ድርጅቱ በ2 ሺህ 500 የኔትወርክ ማማዎች አገልግሎት እየሰጠሁ ነው የሚለው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 500 ያህሉ ራሴ የገነባኋቸው ናቸውም ብሏል፡፡
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎቱን በ280 ከተሞች ማዳረሱን አስታወቀ
የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን በኢትዮ ቴሌኮም እና ሳፋሪኮም መካከል የሚደረጉ ጥሪዎች የጅምላ ዋጋን ከ0.31 ወደ 0.23 ሳንቲም ዝቅ ለማድረግ ያሳለፈውን ውሳኔ እንደሚያደንቅ ሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የቴሌኮም አገልግሎት ነሀሴ 2014 ዓ.ም ላይ በድሬዳዋ ማስጀመሩ ይታወሳል፡፡
ድርጅቱ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ ለ50 በመቶ ህዝብ እንዲሁም በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ውስጥ ደግሞ 98 በመቶ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የቴሌኮም አገልግሎት የመስጠት እቅድ እንዳለው አስታውቋል።
ሳፋሪኮም ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ቮዳኮም ግሩፕ፣ ቮዳፎን ግሩፕ፣ ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽንና ሲዲሲ ግሩፕን ያካተተ ነው።