ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ “ከሚያዝያ አንድ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት እጀምራለሁ” አለ
በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት 7 ሺህ የኔትዎርክ ማማዎችን እንደሚገነባም አስታውቋል
ሳፋሪኮም በቀጣዮቹ አምስት አመታት ከ50 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን የማፍራት እቅድ እንዳለው አስታውቋል
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎቶችን መጀመር ስለሚችልባቸው ሁኔታዎች ለብዙሀን መገናኛዎች ማብራሪያ ሰጥቷል።
በድርጅቱ የቴክኖሎጂ ቺፍ ኦፊሰሩ ፔድሮ ራባካል በዚህ ጊዜ እንዳሉት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከፊታችን ከሚያዝያ 1 ቀን 2014 ጀምሮ የተመረጡ የቴሌኮም አገልግሎቶችን መስጠት ይጀምራል።
የጽሁፍ አገልግሎት፣ የዳታ፣ የድምጽ በአገር ውስጥ እና አለም አቀፍ የቴሎኮም አገልግሎቶችን ይሰጣል ያሉት ቺፍ ኦፊሰሩ ከሰኔ በኋላ ደግሞ ሁሉንም የቴሌኮም አገልግሎቶችን መስጠት ይጀመራልም ብለዋል።
አዲስ አበባ፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ ኮምቦልቻ፣ ሀረር፣ ድሬዳዋ እና ጅግጅጋ አገልግሎቶቹ ከሚጀመርባቸው አካባቢዎች ዋነኞቹ ናቸውም ተብሏል።
በያዝነው የፈረንጆቹ 2022 ዓመት ውስጥ ሁለት ተጨማሪ የመረጃ ማዕከላት በአዲስ አበባ እና አዳማ ከተሞች እንደሚገነባም ድርጅቱ አስታውቋል።
በአጠቃላይ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ውስጥ ለግማሹ ህዝብ የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት እቅድ እንዳለው የገልጸው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፤ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ውስጥ ደግሞ 98 በመቶ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን አገልግሎት የመስጠት እቅድ አለኝም ብሏል።
የኢትዮ ቴሌኮምን የቴሌኮሙንኬሽን መሰረተ ልማቶች ለመጠቀም ድርጅቱ ድርድሮችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።
ሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ ለደንበኞቹ በ07 መነሻ ኮድ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታውቋል።