ሳልቫ ኪር የመከላከያ እና የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ከሃላፊነት አነሱ
የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች አለመግባባት ሀገሪቱን በድጋሚ ወደ ቀውስ እንዳያስገባት ስጋት ፈጥሯል
የፕሬዝዳንቱ እርምጃ የሰላም ስምምነቱን የሚጻረር ነው ተብሏል
ደቡብ ሱዳን በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠ መንግስት እስኪቋቋም ድረስ በስልጣን ላይ ያለው የሽግግር መንግስት በታህሳስ 20 ቀን 2024 ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ በስልጣን ላይ ይቆያል መባሉ አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጅ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሪክ ማቻር ጋር የተፈራረሙትን የሰላም ስምምነት የሚጻረር እርምጃ መውሰዳቸው እየተነገረ ነው፡፡
ሳልቫ ኪር የመከላከያ እና የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሮችን ከስልጣናቸው ያባረሩ ሲሆን ውሳኔው በሀገሪቱ ሰላም ለማምጣት የተደረሰውን “የሰላም ስምምነት የሚጥስ ነው” ተብሏል፡፡
- ፕሬዝደንቱን የሚያሳይ ያልተገባ ቪዲዮ ለቀዋል የተባሉት የደቡብ ሱዳን ጋዜጠኞች ታሰሩ
- የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ ከ2 ሚሊየን በላይ ዜጎች እንዲመለሱ አሳሰቡ
ከስልጣን የተባረሩት የመከላከያ ሚኒስትር አንጀሊና ቴኒ የማቻር ባለቤት ሲሆኑ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደግሞ ማህሙድ ሰለሞን ናቸው።
ሮይተርስ እንደዘገበው ፕሬዝዳንት ኪር የሰላም ስምምነቱን የጣሱት በስምምነቱ መሰረት የማቻር ፓርቲ የተሰጠውን የመከላከያ ሚኒስቴር ኃላፊነት ወደ ፓርቲያቸው እንዲሁም በምትኩ የፓርቲያቸው የነበረውን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርነት ወደ ማቻር በማዛወር ነው።
የማቻር ቃል አቀባይ ፑክ ቦቱስ ባሉንግን "የሚኒሰቴር መስርያ ቤቶቹ መቀየያር... የተደረሰውን ስምምነት የጣሰና በአንድ ወገን በተናጠል የተወሰደ እርምጃ ነው " ብለዋል።
የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች አለመግባባት ሀገሪቱን በድጋሚ ወደ ቀውስ እንዳያስገባት ስጋት ፈጥሯል፡፡
በቅርቡ ሀገሪቱን የጎበኙት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ የደቡብ ሱዳን መሪዎች ካለፈው ትምህርት ወስደው ለሰላም እንዲፈጥሩ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡
-የ86 አመቱ አባ ፍራንሲስ አርብ እለት በጁባ በሚገኘው ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግስት ባደረጉት ንግግር “የሰላምና እርቅ ሂደት አዲስ ጅምርን ይፈልጋል” ሲሉ በአዲሲቷ ሀገር ግጭትን ለማስቆም የተጠናከረ ጥረት እንዲደረግ ጠይቀዋል።
አባ ፍራንሲስ ለደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ባቀርቡት ተማጽኖም "ከእንግዲህ ወዲህ ደም መፋሰስ፣ ግጭት ፣ ሁከትና የእርስ በርስ መገዳደል የለም፣ ከአሁን በኋላ ህዝቦቻችሁ የሰላም ጥማት አይኑርባቸው" ብለዋል፡፡