የህግ ማሻሻያው እንዲደረግ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ተቀዳሚ ምክትላቸው ዶ/ር ሪክ ማቻር ወስነዋል
ደቡብ ሱዳን የሀገሪቱ የብሄራዊ ደህንነት ሰዎች ያለፍርድ ቤት ማዘዣ ዜጎችን እንዲያስሩ የሚፈቅደውን ህግ ልትሰርዝ ነው፡፡
የህግ ማሻሻያው እንዲደረግ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ተቀዳሚ ምክትላቸው ዶ/ር ሪክ ማቻር መስማማታቸውም ነው የተገለጸው፡፡
የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ማርቲን ኤሊያ ሉሞሮ “ቀድሞውንም ቢሆን አለመጋባበት የነበረበት የብሄረዊ ደህንነቱ ህግ (አንቀጽ 54 እና 55) ለመሰረዝ ፕሬዝዳንቱ እና ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ወስነዋል” ብለዋል።
እንደፈረንጆቹ በመስከረም 2019 የተሻሻለው የብሔራዊ ደህንነት አገልግሎት ሕግ፤ የደህንነት ሰዎች ማንኛውንም ሰው ያለፍርድ ቤት ማዘዣ እንዲያስሩ ስልጣን የሰጠ ነበር፡፡
ይህም መጠነ ሰፊ በሆነ የሰብአዊ መብት ረገጣ የሚከሰሰውን የሀገሪቱ የደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤት የሚቀርቡበትን ትችቶች ዝም ለማስባል የተጠቀመው ዜደ ነው በሚል የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ሲገልጹት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡
የህግ ማሻሻያው የመጣው የሀገሪቱ የሽግግር መንግስት የሁለት አመቱን ፍኖተ ካርታን ትግበራ መጀመሩን ይፋ ባደረገበት በዛሬው እለት ነው፡፡
ደቡብ ሱዳን በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠ መንግስትን እንዲኖር የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ይፋ ያደረገችው በወርሃ ሃምሌ 2022 ላይ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
የሽግግር መንግስቱ ለሚቀጥሉት ሁለት አመታት ወይም በታህሳስ 20 ቀን 2024 ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ በስልጣን ላይ እንደሚቆይ ማስታወቁም ይታወሳል፡፡