ፕሬዝደንቱን የሚያሳይ ያልተገባ ቪዲዮ ለቀዋል የተባሉት የደቡብ ሱዳን ጋዜጠኞች ታሰሩ
የደቡብ ሱዳን የጋዜጠኞች ህብረት ምርመራው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ጠይቋል
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ (ሲፒጄ) ጋዜጠኞቹ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መለቀቅ አለባቸው ብሏል
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንትሳልቫ ኪር ሱሪያቸው ረጥቦ የሚያሳይ ቪዲዮ ተጠቅሟል የተባሉት 6 የደቡብ ሱዳን ጋዜጠኞች በጽጥታ ኃይሎች መታሰራቸው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ (ሲፒጄ) ገለጸ፡፡
ያልተገባ የፕሬዝዳንቱን ቪዲዮ አሳይተዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ጋዜጠኞች በደቡብ ሱዳን የሚተዳደረው የደቡብ ሱዳን ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኤስኤስቢሲ) ሰራተኞች መሆናቸውም ነው የተገለጸው፡፡
ሲፒጄ የሚዲያ ዘገባዎችን እና ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሰዎችን ጠቅሶ እንደገለጸው ከሆነ እስረኞቹን የቴክኒክ ክፍል ዳይሬክተር ጆቫል ቶምቤ፣ የካሜራ ኦፕሬተርና ቴክኒሻን ቪክቶር ላዶ፣ የካሜራ ኦፕሬተሮች ጆሴፍ ኦሊቨር እና ጃኮብ ቤንጃሚን፣ የካሜራ ኦፕሬተርና ቴክኒሻን ሙስጠፋ ኦስማን እንዲሁም የቁጥጥር ክፍል ቴክኒሻን ቸርቤት ሩበን የተባሉ ባለሙያዎች ናቸው፡፡
የሲፒጄ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ተወካይ ሙቶኪ ሙሞ እስሩ በዘፈቀደ የተደረገው የእስር ዘመቻ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
"ባለስልጣናት እነዚህን ስድስት የኤስኤስቢሲ ሰራተኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መልቀቅ ና ያለ ተጨማሪ ማስፈራራት እና የእስር ማስፈራሪያ መስራት እንደሚችሉ ማረጋገጥ አለባቸው"ም ብለዋል ሙሞ፡፡
በተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) ምክንያት ጋዜጠኞች እንደታሰሩ የሚገልጸውን ዘገባ በመጀመሪያ ውድቅ ያደረገው የደቡብ ሱዳን የጋዜጠኞች ህብረት (UJOSS) በበኩሉ ምርመራው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ጠይቋል።
“በመጀመሪያ ደረጃ የባለሙያ ጥፋት ወይም ጥፋት ካለ ባለስልጣናቱ ጉዳዩን በፍትሃዊ፣ ግልጽ በሆነ እና በሕጉ መሰረት ለመፍታት አስተዳደራዊ ወይም ሕጋዊ ሂደትን ያፋጥኑ” ሲልም ጠይቋል ህብረቱ፡፡
የሱዳን ፖስት ገለልተኛ የዜና ድረ-ገጽ ማንነታቸው የማይታወቅ የመንግስት ቴሌቪዥን ሰራተኛን በመጥቀስ እንደዘገበው ፖሊስ የኪርን ሽንታቸው ሲለቁ የሚመስል ክስተት የቀረጸው ጋዜጠኛ ሲፈልግ ቆይቷል።
የሱዳን የጸጥታ ኃይሎች የጠረጠሯቸው ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር ቢያውሉም፤ አንድ የኤስኤስቢሲ ባለስልጣን ታማዙጅ ለተባለ ሬድዮ በሰጡት መረጃ የቴሌቭዥን ጣቢያው የተባለውን የሳልቫ ኪር ምስል አየር ላይ እንዳልዋለ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ለጋዜጠኞቹ እስር ምክንያት የሆነው ተንቀሳቃሽ ምስሉ ባለፈው ወር በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሰፊው ሲሰራጭ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ይህም የ71 አመቱ ፕሬዝዳንት የጤና ሁኔታ እና ከግጭት፣ ከረሃብ እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የምትታገል ሀገርን ለማስተዳደር ብቃት ላይ ጥያቄዎችን አስነስቷል።
በሌላ በኩል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንደዚህ ያሉ ምስሎችን በመለጠፍ ስነ ምግባር ላይ እና ለሽማግሌው ያለ ርህራሄ ማጣት ላይ ከባድ ክርክር አስነስቷል።
ሳል-ቫኪር እንደፈረንጆቹ ከ2011 ጀምሮ ደቡብ ሱዳንን እየመሩ ቢሆንም በሀገሪቱ የሚስተዋለው የፖለቲካ ቀውስ የሀገሪቱን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ማነቆ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ለድርድር ዓመታት የፈጀባቸው የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች በመጨረሻም በ2024 ምርጫ ለማድረግ የሚያስችላቸው ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተው የሀገሪቱን መጻኢ እድል ለመወሰን ከስምምነት የደረሱት በቅርቡ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡