ደቡብ ሱዳን ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ 40 ቢሊዬን ገደማ የሃገሪቱን ፓውንድ አጥታለች
ሳልቫኪር ሶስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን አሰናበቱ
የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት የፋይናንስና ኢኮኖሚ ሚኒስትሩን ሳልቫቶር ጋራንግ ማቢዮርዲትን ከስልጣን አነሱ፡፡
ኪር የገቢዎችባለስልጣን ኮሚሽነር ጄነራል ኤርጆክ ቡለንን እና የብሄራዊው ናይል ፔትሮሊዬም ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ቾል ዴንግ (ዶ/ር)ንም ነው ከኃላፊነት ያነሱት፡፡
ባለስልጣናቱ ከኃላፊነት የተነሱበት ምክንያት በውል ባይገለጽም ሃገሪቱ ከገጠማት ከባድ ምጣኔ ሃብታዊ ድቀት ጋር እንደሚያያዝ በሃገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ በተነበበ መግለጫ ተጠቁሟል፡፡
አይ ሬዲዮን መሰል የሃገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች ደግሞ ከሙስናና እና ተያያዥ የፋይናንስ አስተዳደር ችግሮች ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ዘግበዋል፡፡
መጠየቅ አለባቸው የሚሉ አስተያየቶች ከአሁን ቀደም ከታዋቂ አክቲቪስቶች ሲሰነዘሩም ነበሩ፡፡
ፎቶ፡ ኮሚሽነር ጄነራል ኤርጆክ ቡለን
ኮሚሽነር ጄነራል ቡለን ደቡብ ሱዳን ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ 40 ቢሊዬን ገደማ የሃገሪቱን ፓውንድ ማጣቷን ለሃገሪቱ ምክር ቤት አስታውቀዋል፡፡
ይህ ከታክስ ስወራዎች ጋር እንደሚያያዙም ነበር የገለጹት፡፡
ይህ ሃገሪቱን የምንዛሬ ክምችት ከማሳጣቱም በላይ የብሩን የመግዛት አቅም አዳክሞታል፡፡
በዚህም ቡለን በቀድሞው የማሪዲ ክልል አስተዳዳሪ አፍሪካኖ ሞንዴ፣ ቾል ዴንግ ደግሞ በቦል ሪንግ ተተክተዋል፡፡
ከነዳጅ ውጭ በተገኙ ገቢዎች የባንክ ዝውውር የሚጠረጠሩት ማቢዮርዲት በምክትላቸውና ለረዥም አመታት በሚኒስቴሩ ባገለገሉት አቲያንግ ዲንግ እንዲተኩም ፕሬዝዳንቱ አዘዋል፡፡