“በደቡብ ሱዳን በኩል ኢትዮጵያን እጎዳለሁ የሚል ካለ ጸቡ ከእኛ ጋር ነው” ም/ል አምባሳደር ዴቪድ ደንግ
ደቡብ ሱዳን ለግብጽ ወታደራዊ ቦታ ሰጠች መባሉን ሀገሪቱ አጣጥላለች
የግድቡ ጉዳይ በአፍሪካ ማለቅ ሲገባው ጉዳዩን ኒውዮርክ መውሰድ አግባብ እንዳልሆነ በኢትዮጵያ የደ/ሱዳን ም/ል አምባሳደር ገለጹ
“በደቡብ ሱዳን በኩል ኢትዮጵያን እጎዳለሁ የሚል ካለ ጸቡ ከእኛ ጋር ነው” ም/ል አምባሳደር ዴቪድ ደንግ
“ግብጽ በደቡብ ሱዳን ወታደሮችን እያሰለጠነች ነው” የሚሉ ዘገባዎች ባለፉት ሳምንታት ወጥተው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ዘገባዎቹ በዋናት ሲሰራጩ የነበረው በአልጄዚራና በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ነበር፡፡ ከዚህ ባለፈም ደቡብ ሱዳን ለግብጽ የወታደር ማሰልጠኛ ቦታ ፈቀደች የሚሉና ሌሎችም ጁባን ፣ አዲስ አበባንና ካይሮን የሚመለከቱ ዘገባዎች መውጣታቸው ይታወሳል፡፡
ይህንን ተከትሎ በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ደቡብ ሱዳን ምንም አይነት የወታደር ማሰልጠኛ ቦታን ለግብጽም ሆነ ለየትኛውም ሀገር አለመስጠቷን ዜናዎቹም ውሸት መሆናቸውን መግለጹ ይታወቃል፡፡ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ጉዳዩ ፍጹም ከእውነት የራቀ ስለመሆኑ ገልጿል፡፡
ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ምክትል አምባሳደር ዴቪድ ደንግ ኮንግ በደቡብ ሱዳን ውስጥ አንድም የግብጽ ወታደር አለመኖሩን እና ምንም አይነት መሬት ለየትኛውም ሀገር አለመሰጠቱን አረጋግጠዋል፡፡
በደቡብ ሱዳን በኩል አድርጎ ኢትዮጵያን ሊጎዳ የሚችል የትኛውም ሃይል በሀገራቸው ተቀባይነት እንደሌለው ያነሱት አምባሳደር ዴቪድ ደንግ ኢትዮጵያ ጎረቤታችን ብቻ ሳትሆን ሁሉም ነገራችን ናት ብለዋል፡፡
“ከኢትዮጵያ ጋር ድንበር ብቻ አይደለም የምንጋራው” ያሉት ዲፕሎማቱ “ህዝባችን ፣ ባህላችን ፣ ቋንቋችን እና ሌሎች ነገሮቻችንም የተያያዙና የተሳሰሩ ናቸው” ብለዋል፡፡ “በደቡብ ሱዳን በኩል ኢትዮጵያን እጎዳለሁ ብሎ ያሰበ ሃይል በቅድሚያ የሚጣላው ከደቡብ ሱዳን ጋር ነው” ሲሉም ምክትል አምባሳደሩ ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
“የትኛውም አካል ኢትዮጵያን በደቡብ ሱዳን በኩል ሊያጠቃ እንደማይችል የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማረጋገጡንም ነው የገለጹት፡፡
“የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት የሰላም ጸር የሆኑ ሰዎች የሚነዙት ወሬ ብዥታን ሊፈጥር አይገባም” ብለዋል ምክትል አምባሳደሩ፡፡
ከሰሞኑ የሕዳሴ ግድብን ድርድር በሚመለከት ግብጽ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት መውሰዷ አግባብ እንዳልሆነ የገለጹት የደቡብ ሱዳን ምክትል አምባሳደር ጉዳዩ በአፍሪካ ማለቅ ሲገባው ወደ ኒውዮርክ መውሰዱ ትክክል እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡
አምባሳደር ዴቪድ ደንግ አዲስ አበባም ሆነ ካይሮ የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት መሆናቸውን አንስተው አፍሪካ ህብረትን አልፎ ወደ ተባበሩት መንግስታት መውሰድ አግባብ አይደለም ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያና ግብጽን ያላስማማው ጉዳይ በአፍሪካ ደረጃ ሳይታይ ወደሌላ የዉጭ አካል መወሰዱ ተገቢነት የሌለውና የአፍሪካን ችግር በራስ አቅም ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት የሚጻረር መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡